የአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽን ኮሚሽነር ሁንዴ ከበደ እንደተናገሩት፤ በ2017 በጀት ዓመት በሺዎች የሚቆጠሩ ተሳታፊዎች የነበሯቸው ከ150 በላይ ትላልቅ ሀገር አቀፍ፣ አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ሁነቶች በአዲስ አበባ ከተማ ተካሂደዋል።
ከዚህ በፊት ከአፍሪካ ኅብረትና መሰል ሁነቶች ጋር የሚያያዙ ካልሆኑ በቀር በዚህ ቁጥር ልክ በከተማዋ የሚስተናገዱ ኩነቶች እንዳልነበሩ አስታውሰዋል፡፡
የኮሪዶር ልማቱ የአዲስ አበባን መልክ መቀየሩን ገልጸው፤ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች የተሠሩት የኮሪዶር ልማቶች የልማት ጥያቄን ከመመለስና ተጨማሪ የቱሪስት መዳረሻዎችን ከመፍጠር በዘለለ ከተማዋ ራሷ የቱሪስት ማዕከል እንድትሆን አድርጓታል።
እንደ ኮሚሽነር ሁንዴ ገለጻ፤ የከተማዋን መቀየር ተከትሎ በብዛት እየመጡ ያሉት አህጉር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ሁነቶች አዲስ አበባ ላይ ሲዘጋጁ ለሆቴሎች ትልቅ የሥራ ዕድል ይፈጠርላቸዋል።
ኮሚሽነሩ የዓድዋ ድል መታሰቢያ፣ አንድነት ፓርክ፣ ወዳጅነት ፓርክ፣ ሳይንስ ሙዚየም፣ ብሔራዊ ቤተመንግሥት፣ እንጦጦ ፓርክ፣ አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ሴንተር እንዲሁም ብሔራዊ ሙዚየም እና አዲስ አበባ ሙዚየምን ጨምሮ የኮሪዶር ልማቱ ለዕይታ ያበቃቸው የቱሪስት ፍሰት እንዲጨምር ማድረጋቸውን ተናግረዋል ሲል የዘገበው ኢፕድ ነው፡፡












