የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በመጪዎቹ ቀናት ለመገናኘት መስማማታቸውን ክሬምሊን አስታውቋል።
ትራምፕ ከሩሲያ እና ዩክሬን አቻዎቻቸው ጋር በአካል ተገናኝተው በቅርብ ጊዜ በዩክሬን እና ሩሲያ መካከል ያለውን ጦርነት ለማቆም ለመወያየት ጥሩ እድል አለ ማለታቸውን ተከትሎ ነው። ትራምፕ በዋይት ሀውስ ባደረጉት ንግግር ዘለንስኪ እና ፑቲን የሶስትዮሽ የመሪዎች ስብሰባ ላይ ለመገኘት ማሰባቸው ለሚደረገው ምክክር ተስፋ ሰጪ ነው ብለዋል።
የክሬምሊን ረዳት ዩሪ ኡሻኮቭ የሶስትዮሽ የመሪዎች ጉባኤ ሃሳብ በሞስኮ በተደረጉ ውይይቶች ላይ መጠቀሱን ገልጸው ትራምፕ እና ፑቲን ለመገናኘት ስምምነት ላይ መደረሱን እንዲሁም ተጨማሪ ዝርዝሮችን ይፋ እንደሚሆኑ ገልጸዋል።
ዘለንስኪ በኤክስ ገጻቸው ላይ እዳሰፈሩት፤ እውነተኛ መፍትሄዎችን ማፈላለግ ውጤታማ እንደሚሆን ደጋግመን ተናግረናል በማለት ዩክሬን ለጉባኤው ያላትን ድጋፍ አመልክተዋል። በትራምፕ እና በፑቲን መካከል ሊኖር የሚችለው ስብሰባ የአሜሪካው ተወካይ ስቲቭ ዊትኮፍ ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ጋር መነጋገራቸውን ተከትሎ ነው።
የዘገበው ቢቢሲ ነው
በ – ሔርሜላ ተመስገን












