የጎንደር ዩኒቨርሲቲ 70ኛ እና የማስተማሪያ ሆስፒታሉን 100ኛ ዓመት ክብረ በዓል የጀመረውን የማህበረሰብ አገልግሎትና የምርምር ልህቀት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትና አሁን ባገኘው ስኬት እንዳይዘናጋም ሚኒስትሩ አሳስበዋል፡፡
ፕሮፌሰር ብርሃኑ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቤተሰብ ቃልኪዳን የዩኒቨርሲቲውንና የማህበረሰቡን ትስስር የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል፡፡
ከየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል የመጣ ተማሪ በጎንደር እናቶች እንደ ልጃቸው ሲታይ የዩኒቨርሲቲውን ዜጋ ተኮር ሥራ ያሳያል፤ ለሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችም አርዓያ ሊሆን ይገባል ነው ያሉት፡፡
ዩኒቨርሲቲው የቀድሞ ተመራቂዎቹን ማሰባሰቡ ከተማረው ዜጋ ጋር ያለውን ትሰስር የሚያጠናክርና ከማህበረሰብ ጋር ያለውን ቅርበት ያሳያል ብለዋል፡፡
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ ዩኒቨርሲቲዎች መወዳደር ያለባቸው በሚፈጥሩት የሰለጠነ ዜጋ፣ እውቀትና ፈጠራ ያለው ዜጋ እንጂ በሕንጻ ብዛትና በግቢ ስፋት መሆን የለበትም ብለዋል፡፡
የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ዋነኛ ውጤት የማህበረሰብ ችግር ፈቺ መሆን እና ለሀገር ዕድገትና ሥልጣኔ የሚሆን ብቁ ዜጋ መፍጠር ነው ብለዋል፡፡ “እንደ ሀገር ያሉ ችግሮችን መፍታት የሚቻለው ችግር ፈቺ ማህበረሰብ ሲፈጠር ነው” ያሉት የትምህርት ሚኒስትሩ፤ ለዚህም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ቆራጥ ውሳኔ እና ፈጣን ለውጥ ማምጣት እንደሚጠብቅባቸው ተናግረዋል፡፡
መንግሥት ትኩረት ከሚሰጣቸው ጉዳዮች ትምህርት ቀዳሚውን ድርሻ እንደሚወስድም ተናግረዋል፡፡ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ 70ኛ እና የማስተማሪያ ኮሌጁን 100ኛ ዓመት ያከበረው በርካታ ፕሮጀክቶችን በማስመረቅ ነው ብለዋል፡፡
በክብረ በዓሉ ማጠናቀቂያ መድረክ 25 ፕሮጀክቶችን ለመሥራት የመሰረት ድንጋይ በማስቀመጥ ነው፤ ለዚህም ከትምህርት ሚኒስቴር በጀት ሳይጠይቅ ነው ብለዋል። “ይህ ደስ የሚል እና ሌሎችም ሊማሩበት የሚገባ ነው” በማለት ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ “ዳሩ ግን የሚፈፀም ከሆነ ነው” ብለዋል። ዩኒቨርሲቲዎች ከማክበርና በትንሽ ስኬት ከመኩራራት ወጥተው አገር የሚለውጥ ሥራ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።
ሔርሜላ ፈቃደ (ጎንደር)












