በመካከለኛው ቻይና ሁናን ግዛት የምትኖር የ16 ዓመት ልጃገረድ፣ ክብደትን በፍጥነት ለመቀነስ አደገኛ የአትክልት አመጋገብን እና “ላክሲቲቭ” በመባል የሚታወቀውን የተቅማጥ መድሃኒት በመጠቀሟ ህይወቷን አደጋ ላይ ጥላለች፡፡
ለሁለት ሳምንታት ያክል የአትክልት ምግቦችን ብቻ ስትመገብ እንዲሁም “የላክሲቲቭ”መድሃኒቶችን ስትወስድ እንደነበር ቤተሰቦቿ የገለጹ ሲሆን፣ በዚህም ሳቢያ የእጆቿ እና የእግሮቿ ጥንካሬ መቀነሳቸውን እንዲሁም የትንፋሽ እጥረት ስላጋጠማት ወደ ሆስፒታል ተወስዳለች ብለዋል።
በተደረገላት ምርመራም “የፖታስየም” መጠኗ ወደ አደገኛ ደረጃ ወርዶ ከባድ “ሃይፖካላሚያ” የሚባል በሽታ ያጋጠማት ሲሆን፣ በተጨማሪም ለሕይወት አስጊ የሆነ የመተንፈሻ አካላት ችግር እና ድንገተኛ የልብ ድካም እንዳስከተለባት ተገልጿል፡፡
የልደት ቀኗን አለባበስ ለማስተካከል በሚል ምክንያት ክብደት ለመቀነስ በማሰብ ለሁለት ሳምንታት በአትክልት አመጋገብ እና “ላክሲቲቭ” መድሃኒትን ስትወስድ እንደቆየች ለህክምና ባለሞያዎች ተናግራለች።
በተአምር አገግማ በቅርቡ ከሆስፒታል እንደወጣች የገለጹት ዶክተሮቹ፣ ለጤንነታቸው ሳያስቡ በፍጥነት ክብደታቸውን ለመቀነስ ለሚፈልጉ ሌሎች ሰዎች ማስጠንቀቂያም ሰጥተዋል።
በ-ሔርሜላ ተመስገን












