የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዚም ቢሮ በተያዘው በጀት ዓመት የሻደይ፣ አሸንድዬና ሶለል በዓላትን በዩኒስኮ ለማስመዝገብ በትኩረት እንደሚሰራ አስታወቀ፡፡
በዓላቱ ሀይማኖታዊና ባህላዊ ትውፊታቸውን ጠብቀው እንዲከበሩ የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑም ተመላክቷል፡፡
የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ አባይ መንግስቴ እንዳሉት፣ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የአሸንድዬ፣ ሻደይ፣ ሶለል፣ የእንግጫ ነቀላ፣ የቡሄ እና ሌሎች ባህላዊና ሀይማኖታዊ በዓላትን በድምቀት ለማክበር ከወረዳ ጀምሮ የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተሰሩም ነው፡፡
ከነሀሴ 16 ጀምሮ በዋግሕምራ፣ በሰሜን ወሎ፣ በጎንደር፣ በጎጃምና በሌሎች አካባቢዎች እንደሚከበሩ አስታውቀዋል፡፡ በዓላቱ የማህበረሰብ በዓል በመሆናቸው ትውፊታቸው ተጠብቆ እንዲከበሩ ማድረግ ይጠበቅብናል ያሉት አቶ አባይ፤ በዚህም ኮሚቴ ተቋቁሞ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኝ አመላክተዋል፡፡
የሻደይ፣ አሸንድዬና ሶለል በዓላትን በዓለም አቀፍ የማይዳሰሱ ቅርሶች ለማስመዝገብ ከዚህ በፊት የተጀመረ ጥረት መኖሩን አስታውሰው፤ በተያዘው ዓመት እንዲመዘገቡ ለማድረግ በትኩረት ይሰራል ነው ያሉት፡፡
በተጨማሪም በበዓላቱ የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎች እንዲታደሙ ለማድረግ የማስተዋወቅ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡












