ከጅቡቲ ዶላሬ ወደብ የተነሳችው ጣናነሽ ቁጥር-2 ጀልባ የየብስ ጉዞዋን ልታጠናቅቅ ወደ ባህርዳር እየተጠጋች ነው።
38 ሜትር ርዝመት ያላት እና በአንድ ጊዜ 188 ሰዎችን የመጫን አቅም ያላት ጣናነሽ-2 ጀልባ በሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎች ላይ ያደረገችውን የየብስ ጉዞ አጠናቅቃ መዳረሻዋ ወደሆነችዉ ዉቢቷ ባህርዳር ተቃርባለች።
የከተማዋ ህዝብም ደማቅ አቀባበል አያደረገላት ይገኛል። የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው የከተማዋ መሪዎች እና ነዋሪዎች ለባሕር ዳር ከተማ ተደማሪ ውበት የምትኾነዋን ጀልባ ለመቀበል ዝግጅት ሲያደርጉ ቆይተዋል ብለዋል።
“ጣናነሽን በክብር መቀበል በፍቅር የሸኙልንን ኢትዮጵያውያን ማክበርም ነው” ያሉ ከንቲባው ጀልባዋ የመተሳሰብ፣ የአንድነት እና የፍቅር ተምሳሌት ናት ብለዋል። ለታላቁ ጣና ሐይቅ እና ለባሕር ዳር ከተማ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ጉልህ ሚና የምትጫዎት ስለመኾኑም ገልጸዋል።
ለበርካታ ዓመታት በጣና ሐይቅ ላይ አገልግሎት እየሰጠች የምትገኘው ጣና ነሽ ቁጥር፩ ጀልባ ላለፉት በርካታ ዓመታት ለማህበረሰቡ በትራንስፖርቱ ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶችን እየሰጠች እንደምትገኝም ነዋሪዎች ገልፀዋል።
ጣናነሽ ቁጥር ፪ ጀልባ ወደ ስራ ስትገባ ለማህበረሰቡ የምትሰጠው ጠቀሜታ ዘርፈ ብዙ ነው። በተለይ በከተማዋ ለቱሪዝሙ ዘርፍ ማደግ የሚኖራት አበርክቶም ከፍተኛ መሆኑን ነዋሪዎች ተናግረዋል።












