ደኖችን ወደ ነበሩበት የመመለስ ስራ የሰው ልጆች ቀዳሚ ስራ መሆን አለበት ሲሉ የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገለጹ።
የትምህርት ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት አመራርና ሰራተኞችም በመዲናዋ በግንፍሌ ወንዝ ዳር ፕሮጀክት አካባቢ ችግኝ ተክለዋል፡፡ ለትምህርት ከምንሰጠው ትኩረት ባልተናናሰ የአየር ንብረቷ የተስተካከለ ሀገር ለትውልዱ ለማስረከብ የሚሰራውን ተግባር ማጠናከር አለብን ነው ያሉት።
የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴ በበኩላቸው፤ ባለፉት አመታት የተተከሉት ችግኞች ለአካባቢ፣ ለአየር ንብረት ጥበቃና ለኢኮኖሚ ዕድገት ፋይዳቸው የላቀ ነው ብለዋል። በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የተያዘውን ግብ ለማሳካት ችግኞችን መትከል ብቻ ሳይሆን የጽድቀት መጠናቸው እንዲጨምር የችግኞች እንክብካቤ ላይ በደንብ መስራት አለብን ነው ያሉት።
በትምህርት ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት ላለፉት አመታት የተተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ በኩልም በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸው አብዛኞቹም መጽደቃቸውን አክለዋል።












