NBC Ethiopia
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር እና የአፈርና ውሀ ጥበቃ ተግባራት በየዓመቱ በመሸርሸር ወደ ሀይቆችና ወንዞች የሚገባውን 1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ሜትሪክ ቶን አፈር ወደ 208 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ዝቅ ማድረግ መቻሉን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።
በዘንድሮው 7ኛ ዙር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር “በመትከል ማንሰራራት” በሚል መሪ ሀሳብ 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ዕቅድ ተይዞ እስካሁን 5 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኞች ተተክለዋል።
በግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም መሪ ሥራ አስፈፃሚ ፋኖሴ መኮንን፤ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር ከችግኝ ተከላ ባለፈ የኢኮኖሚና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
በአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር ለደንና ጥምር ደን አገልግሎት የሚውሉ ችግኞች እንደሚተከሉ ገልጸው፤ በአረንጓዴ ዐሻራ እና በአፈርና ውሀ ጥበቃ ተግባራት ከ33 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት እንዲያገግም ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር እና ሥነ አካላዊ የአፈርና ውሀ ጥበቃ በየዓመቱ በመሸርሸር ወደ ሀይቆችና ወንዞች የሚገባውን አንድ ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ማትሪክ ቶን አፈር ወደ 208 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ዝቅ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።
ከእርሻ መሬት ላይ በየዓመቱ ይሸረሸር የነበረውን 130 ቶን አፈር ወደ 54 ቶን ዝቅ ማድረግ መቻሉንም ተናግረዋል።
አክለውም በገላጣ መሬት ላይ በየዓመቱ ይሸረሸር የነበረውን 300 ቶን አፈር ወደ 91 ቶን ዝቅ እንዲል መደረጉን ገልጸዋል።












