አርሰናል ኤበርቺ ኤዜን ለማስፈረም ካሉት ተጫዋቾች የመሸጥ ግዴታ ይጠብቀዋል ተባለ።
የሰሜን ለንደኑ ክለብ በያዝነው የዝውውር ገበያ 5 አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ቡድን ስብስቡ መቀላቀሉ ይታወሳል። አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ ከቀናት በፊት በሰጠው አስተያየት ክለቡ አሁንም ተጫዋች እንደሚያስፈርም ፍንጭ መስጠቱም አይዘነጋም።
የመድፈኞቹ ቀጣዩ ኢላማ የክሪስቲያል ፓላሱ የክንፍ ተጫዋቹ ኤበርቺ ኤዜ ነው የተባለ ሲሆን፣አርሰናል ተጫዋቹን የግሉ ለማድረግ ካለው የቡድን ስብስብ አንድ ወይም ሁለት ተጫዋች መሸጥ ይኖርበታል ተብሏል።
አርሰናል የኤዜን በፓላስ ቤት ያለውን የውል ማፍረሻው 60 ሚሊዮን ፓውንድ መክፈል ቢችልም፣በአንድ ምዕራፍ ለመክፈል የፋይናንስ ጨዋነት ደንቡ አንቆ እንደሚይዘው ተዘግቧል። የ27 አመቱ እንግሊዛዊ ወደ መድፈኞቹ መጓዝ እንደሚፈልግ ለጓደኞቹ ተናግሯል የተባለ ሲሆን፣አርሰናልም የያዝነውን የዝውውር መስኮት የመጨረሻው ፈራሚ ሊያደርገው ይፈልጋል ተብሏል።
አርሰናል በቀጣይ ከሊያንድሮ ትሮሳር፣ጋብሬል ጄሱስ ወይንም ኦሌክሳንደር ዚንቼንኮ አንዳቸውን በመሸጥ የኤዜን ዝውውር ያፋጥናል ተብሎ ይጠበቃል።
በ-አልፈሪድ ነስሮ












