በአዲስ አበባ በተለያዩ ክ/ከተሞች የማታለል (የሿሿ) ወንጀሎችን ሲፈፅሙ የነበሩ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የአራዳ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ክ/ከተሞች ወንጀሎቹን በመፈፀም ህዝብን ሲያማርሩ እንደነበር የፒያሳ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ገልጿል፡፡
ግለሰቦቹ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ በመምሰል በለሚ ኩራ፣ በቂርቆስና በአራዳ ክ/ከተሞች ወንጀሎቹን መፈፀማቸውን ህብረተሰቡ ለፖሊስ በተሰጠው ጥቆማ መነሻነት የምርመራ መዝገብ ተደራጅቶባቸው ሲፈለጉም ቆይተዋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በሦስት ዙር በተደረገ ጠንካራ ክትትል በአጠቃላይ 21 ተከሳሾች ለዚሁ ወንጀል ተግባር ሲጠቀሙባቸው ከነበሩባቸው ሦስት ተሽከርካሪዎች ጋር በፒያሳ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ በቁጥጥር ስር ሊውሉም ችለዋል፡፡
በመጀመሪያው ዙር የተያዙት ከዚህ ቀደም ብዛታቸው ዘጠኝ የሆኑ ኮድ – 3 – 78652 ኦሮ ሰሌዳ ተሽከርካሪን በመጠቀም ከዘጠኝ ተጠርጣሪዎች ጋር በመያዝ ክስ መመስረቱን አስቷውሷል፡፡
በሁለተኛው ዙር የተያዙት ደግሞ ብዛታቸው አምስት ሲሆኑ፣ የሠሌዳ ቁጥር ኮድ 3 ኦሮ 42866 ሚኒባስ በመጠቀም ሰኔ 15 ቀን 2017 ዓ/ም በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ልዩ ቦታ ቴዎድሮስ አደባባይ ከቀኑ 5፡00 ሰዓት አካባቢ አቶ ተምትሜ ወልደማርያም የተባሉ የግል ተበዳይ ላይ ወንጀሉ ተፈጽሞባቸዋል፡፡
ተከሳሾቹ የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ በመምሰል ግለሰቡን መኪና ውስጥ በማስገባት፣ ጉሮሮአቸውን በማነቅና ሞባይል ስልካቸውን በመቀማት ትንሽ ከተጓዙ በኋላ ከመኪናው ገፍትረው ጥሏቸዋል፤ ሁኔታውን ያዩ በአካባቢው በስራ ላይ የነበሩ የፖሊስ አባላትም የተሽከርካሪውን ሠሌዳ በመያዝ በተደረገው ክትትል በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
በሦስተኛው ዙር በቁጥጥር ስር የዋሉት ደግሞ ብዛታቸው ሰባት ተጠርጣሪዎች ናአቸው ያለው ፖአሊስ፣ ኮድ 3 ማ/ኢ 01046 ተሽከርካሪን በመጠቀም ሐምሌ 9 ቀን 2017 ዓ/ም በአራዳ ክፍለ ከተማ ቴዎድሮስ አደባባይ አካባቢ የግል ተበዳይ ታክሲ ለመጠቀም ቆመው ባሉበት መኪና ውስጥ ካስገቧቸው በኋላ አንገታቸውን አንቀው የሞባይል ስልካቸውን በመቀማት ከመኪናው ገፍትረው በመጣል ቢያመልጡም፣ ዘረፋው የተፈፀመባቸው ግለሰብ የተሽከርካሪውን ሠሌዳ ቁጥር በመያዝ ለፒያሳ አካባቢ ፖሊስ በመስጠትና ክስ በመመስረት በተደረገው ፍተሻ በቁጥጥር ስር ሊውሉም ችለዋል፡፡
ወቅቱ ክረምትና የዝናብ ወቅት እንደመሆኑ መጠን ወንጀል ፈፃሚዎች አጋጣሚ በመጠቀም የሞላ ታክሲ አስመስለው ከፌርማታ ውጪ ግለሰቦችን ወዴት ናችሁ? ብለው በመጠየቅ የወንጀል ድርጊቱን እየፈፀሙ ይገኛሉ፡፡ የትራንስፖርት ተጠቃሚዎችም ከዝናብ ለመሸሽና ፈጥኖ ትራንስፖርት ለማግኘት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ለወንጀል ተጋላጭ እየሆኑ ስለሚገኙም ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ነው ሲል ፖሊስ አስጠንቅቋል።
በከተማችን አዲስ አበባ ማንም ሰው ወንጀል ፈፅሞ ማምለጥ እንደማይችል ሁሉም ተገንዝቦ ማንኛውም ዓይነት መሰል አጠራጣሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ የተሽከርካሪውን ሠሌዳ ቁጥር በመያዝና በ991 የፖሊስ የመረጃ ስልክ በመደወል ሪፖርት ማድረግ የሚገባ ሆኖ በእነዚህ ተጠርጣሪዎችና ተሽከርካሪዎች ተመሳሳይ ወንጀል የተፈፀመበት ካለም ለአራዳ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ መረጃ መስጠት የሚችል መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ መልዕክቱን ያስተላልፋል፡፡












