ኢትዮጵያ እና ጣሊያን በግብርናው ዘርፍ ትብብራቸውን ማጠናከር የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ዛሬ በአዲስ አበባ ተፈራርመዋል።
ስምምነቱን የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) እና የጣሊያን ግብርና እና ምግብ ሉዓላዊነት ሚኒስትር ፍራንሲስኮ ሎሎ ብሪጅዳ ተፈራርመዋል።
የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ በስምምነቱ ጣሊያን በኢትዮጵያ የቡና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ የቴክኖሎጂ እና የዕውቀት ድጋፍ እንደምታደርግ እንዲሁም ለአርሶ አደሮች የተለያዩ ድጋፎች እንደሚደረጉ አንስተዋል።
የጣሊያን አቻቸው ፍራንሲስኮ ሎሎብሪጊዳ በበኩላቸው ኢትዮጵያ እና ጣሊያን በትብብር 2ኛውን የተመድ የምግብ ሥርዓት ጉባኤን በስኬት ማዘጋጀታቸውን ገልጸው፤ በግብርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ በጋራ መስራት የሚያስችሉ አማራጮች ላይ ስምምነት መፈፀሙን ጠቁመዋል።
ስምምነቱ ሁለቱ ሀገራት ከዚህ በፊት የነበራቸውን ትብብር የሚያጠናክርና በተለይም የቡና ሰንሰለቶችን የማዘመን ስራ ላይ በትኩረት ለመስራት የሚያስችል መሆኑ ተነስቷል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡












