በሀገር ውስጥ የውሃ ትራንስፖርትን ማሳደግ የሚያስችሉ ዘመናዊ ጀልባዎችን ማስገባት መጀመሩን የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አስታወቀ።
የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ዋና ስራ አስፈጻሚ በሪሶ አመሎ(ዶ/ር)፤ በ2017 በጀት ዓመት በተቋሙ የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትን አስመልክተው ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫውም የገቢ መጠን ማሳደግ፣የመርከቦችንና የጭነት ተሽከርካሪዎችን የመጫን አቅም መጨመር፣ ፈጣንና ተደራሽ የሆነ አገልግሎት መስጠትና በቴክኖሎጂ የታገዙ አሰራሮችን ማጎልበት በበጀት ዓመቱ በትኩረት የተከናወኑ ተግባራት መሆናቸውን አንስተዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰቱ አለመረጋጋቶች በባህር ትራንስፖርት አገልግሎት እንቅስቃሴ ላይ የፈጠሩትን ጫና በመቋቋም ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ገልጸዋል። ከዚህ አንጻር በ2017 በጀት ዓመት 101 ነጥብ 86 ቢሊየን ብር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ ከ108 ነጥብ 78 ቢሊየን ብር ገቢ መገኘቱን ገልጸዋል።
የድርጅቱ ገቢ ከፍ እንዲል ተግባራዊ የተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረው ተቋሙ ወጪ ቆጣቢ አሰራር ስርዓቶችን በመዘርጋት የተሰሩ ስራዎች ውጤታማ እንደነበሩም አክለዋል።
በጭነት አስተላላፊ ዘርፍም ከፍተኛ ውጤት የተገኘበት ዓመት ነው ያሉት ዋና ስራ አስፈፃሚው፤ በመልቲ ሞዳል እና በዩኒ ሞዳል ዘርፍ አመርቂ ውጤት መገኘቱን አብራርተዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።












