በሐረሪ ክልል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተመዘገቡ ስኬቶችን ለማጎልበት ይሰራል ሲሉ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሮዛ ኡመር ተናገሩ።
የሐረሪ ክልል የመንግስትና የፓርቲ የ2017 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ እየተካሄደ ነው። የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሮዛ ኡመር እንደገለፁት፤ በተጠናቀቀው የ2017 በጀት ዓመት በክልሉ በሁሉም ዘርፎች አበረታች ተግባራትን ማከናወን ተችሏል።
በተለይም በክልሉ ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ፖለቲካዊ እንዲሁም በከተማ ልማት ዘርፍ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ ተግባራትን ማከናወን መቻሉን ገልፀዋል።
በጀት ዓመቱ የተቋማት አገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን ለማህበረሰቡ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ በመስጠት ተጨባጭ ለውጥ የተመዘገበበት መሆኑንም አክለዋል።
የግምገማ መድረኩም በበጀት ዓመቱ የነበሩ ጠንካራ ጎኖችን በማስፋት የተስተዋሉ ውስንነቶችን በመሙላት የተመዘገቡ ውጤቶችን ለማስፋት ግብዓት ለመሰብሰብ ዝግጅት የሚደረግበት መሆኑን ጠቁመዋል።
በብልፅግና ፓርቲ የሐረሪ ክልል ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ጌቱ ወዬሳ በበኩላቸው፥ በክልሉ የተጠናቀቀው በጀት ዓመት በርካታ ውጤቶች የተመዘገቡበት የትጋትና ስኬት ዘመን እንደነበር አመላክተዋል።
የግምገማ መድረኩ የ2017 ማጠቃለያና በ2018 ዋና ዋና አቅጣጫዎች ላይ ውይይት የሚደረግበት መሆኑንም ጠቁመዋል። የትርክት የበላይነትን ከማስረፅ አንፃር የተከናወኑ ተግባራትም በጥልቀት እንደሚገመገሙ ጠቁመዋል።
በግምገማ መድረኩ ላይ የክልሉ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ሱልጣን አብዱሰላምን ጨምሮ የክልሉ የመንግስትና ፓርቲ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች እየተሳተፉ ነው ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡












