የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን እንቅስቃሴ በግልጸኝነት፣ በተጠያቂነት፣ ዓለም አቀፍ መርሆዎችን እና ሀገራዊ እሴቶችን ያከበረ የአሥተዳደር ሥርዓት እንዲኖራቸው እና ድርጅቶቹን በመወከል ሚናውን እንዲወጣ የሚያስችል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት በባሕር ዳር ተመሥርቷል።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አማካሪ መስፍን አበጀ (ዶ.ር) እንደገለጹት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የመንግሥት ስትራቴጂያዊ አቅም እና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን ባሕል ለማድረግ የማይተካ ሚና አላቸው፡፡
በክልሉም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ የጸደቀ ሲሆን ለአተገባበሩም ሕጋዊ መሠረት ያለው ምክር ቤት ማቋቋም በማስፈለጉ የምሥረታ ጉባኤው ተደርጓል ብለዋል።
የፌዴራል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፋሲካው ሞላ በኢትዮጵያ 5 ሺህ 500 የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች መኖራቸውን ገልጸዋል።
በተፈጠረው ምቹ ኹኔታም 3 ሺህ 400 የሚኾኑት ባለፉት አምሥት ዓመታት ሥራ የጀመሩ መኾናቸውን ጠቅሰዋል። መንግሥት እና ድርጅቶቹ በትብብር እና በቅንጅት የሚሠሩበት ኹኔታ በመፈጠሩ በሥፋት እየሠሩ መኾኑን ገልጸዋል።
የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሪፎርም ዓላማ በእንቅስቃሴያቸው የሕዝብን ችግር ቀርፎ ተጠቃሚነቱን ማረጋገጥ ነው ብለዋል። ለዚህም መንግሥትን ጨምሮ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የባለድርሻ አካላት የትብብር እና የቅንጅት መድረኮች እየተቋቋሙ ነው።
በምሥረታ ጉባኤው ስለ ምክር ቤቱ ዓላማ፣ አደረጃጀት እና አሠራር ውይይት ተደርጓል።












