የዴሞክራሲ ባህልን በመገንባት ጉዳይ ሁላችንም በትብብር በመሥራት አርአያ ሆነን ማሳየትም አለብን ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት እና ሰላም ሚኒስቴር በጋራ “ሰላምን በማጽናት የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና” በሚል መሪ ሀሳብ ያዘጋጁት ሀገር አቀፍ የሰላም ኮንፈረንስ መካሄድ ጀምሯል።
በመድረኩ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የሰላም ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሰለሞን አየለ እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና የዴሞክራሲ ተቋማት አመራሮች ታድመዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ሰላም ለኢትዮጵያውያን ልማትን፣ ፍትሕንና ደስታን ያለምንም ዕንቅፋት የማግኘት ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።
በአገራችን ታሪክ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች፤ ግጭትና መፈናቀል የሰላምን እንቅፋት ሆነው መኖራቸውን አንስተዋል። የለውጡ ዋናው ስትራቴጂ በጉልበት የሚደረጉ ኋላቀር የፖለቲካ ባህልና የሰላም ችግር አፈታት መሆኑን ገልጸዋል።
ሰላምን ለማፅናት የተፈጥሮንም ሆነ የሰውንም ጉልበተኝነት በጋራ መግራት እንደሚገባ ጠቅሰው፤ ዓባይን ገርተን ለኃይል ማመንጫ እንደተጠቀምነው ሁሉ ሌሎችንም የተፈጥሮን ጉልበተኝነትን ገርተን ለልማትና ለብልጽግና ማዋል አለብን ነው ያሉት።
የሰለጠነ የፖለቲካ ሥርዓት ዴሞክራሲያዊ ዕሴቶችን ያዳበረ ሕዝብ እና ዴሞክራሲያዊ ዕሴቶችን የተረዱ ልሂቃንን እንደሚፈልግም ጠቁመዋል።
በመሆኑም ለኢትዮጵያውያን ባህልና ዕሴት የሚስማማ ዴሞክራሲን በጋራ መቀመር እንደሚገባ በማንሳት የፓርቲዎች ፉክክር ብቻ ሳይሆን ትብብርም ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ጠመንጃ እና ጡንቻ ዴሞክራሲን አይገነቡም ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ግጭት ቀስቃሽነት፣ አኩራፊነት፣ ጽንፈኝነት እና እኔ ብቻ ባይነት አላስፈላጊ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣ ሀገራዊ ለዉጡን ተከትሎ የተፈጠረውን የፖለቲካ ምኅዳር ለማስፋት፣ ዘላቂ ለማድረግና የዴሞክራሲ ባህልን ለመገንባት የሚያደርገውን ሚናም አድንቀዋል።
መንግሥት ለሰላም ሁሌም ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸው፥ የፖለቲካ ኃይሎችም ሰላምን ለማጽናት በሚደረገዉ ጥረት ሁሉ የበኩላቸውን አዎንታዊ አበርክቶ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡












