ኢትዮጵያና ቻይና የግብርና ምርታማነትን በሚያሳድጉ አዳዲስ የግብርና ምርምር ቴክኖሎጂዎች ያላቸውን ትብብር የበለጠ እንደሚያጠናክሩ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ከቻይና ሻንጋይ ጂያኦቶንግ ዩኒቨርሲቲ የምግብ ሳይንስና ኢንጅነሪንግ ልኡካን ቡድን ጋር ትብብርን የበለጠ ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርጓል።
ውይይቱ በእውቀት ሽግግር፣ ምርምር፣ የሰው ኃይል ልማት፣ ቴክኖሎጂና ሌሎች የትብብር ዘርፎች ላይ ያተኮረ ሲሆን ለዚህም የሁለትዮሽ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል። የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ንጉሴ ደቻሳ ኢትዮጵያ በግብርና ዘርፍ ያላትን አቅምና ምርታማነትን ለሚያሳድጉ ምርምሮች ትኩረት መስጠቷን አንስተዋል።
የቻይና ሻንጋይ ጂያኦ ቶንግ ዩኒቨርሲቲ የደረሰበት የምርምር ቴክኖሎጂ የግብርና ምርትን በእጥፍ የሚያሳድግ እንደሆነም ገልጸዋል። የቻይና ሻንጋይ ጂያኦቶንግ ዩኒቨርሲቲ ልኡካን ቡድን መሪ ፕሮፌሰር ጁን ሱይ በበኩላቸው ከኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ጋር ያላቸውን ትብብር የበለጠ ማጠናከር እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በግብርና ዘርፍ የተለያየ ስብጥር ያላቸው የሰብል አይነቶች እንዳላት በመጠቆም ጥራትና እሴትን ለመጨመር በምርምርና ቴክኖሎጂ በትብብር እንሰራለን ብለዋል። የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩትና የቻይና ሻንጋይ ጂያኦ ቶንግ ዩኒቨርስቲ ከ6 ዓመት በላይ ያስቆጠረ ትብብር እንዳላቸው ተገልጿል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።












