በያዝነው የተጫዋቾች የዝውውር ገበያ በንቃት እየተሳተፈ የሚገኘው ማንችስተር ሲቲ የበርንሌውን ግብ ጠባቂ ለማስፈረም በሂደት ላይ እንደሚገኝ ዘ አትሌቲክ አስነብቧል።
ጀምስ ትራፎርድ በሲቲ አካዳሚው ውስጥ ከ12 አመቱ ጀመሮ የቆየ ተጫዋች ሲሆን፣ ክለቡ ለበርንሌይ የሸጠው ከሁለት አመት በፊት ነበር። በሁለቱ ክለቦች መካከል አስቀድሞ በተቀመጠ ስምምነት መሰረት ሲቲ እንግሊዛዊውን ግብ ጠባቂ በ40 ሚሊዮን ፓውንድ የማስፈረም መብት ይኖረዋል።
በዚህም መሰረት የኤደርሰን ሞራዬስን ቆይታ ያላረጋገጠው ማንችስተር ሲቲ የመልሶ መግዣ ሂሳቡን ከፍሎ ለማስፈረም በሂደት ላይ እንደሚገኝ እና ከተጫዋቹጋም በግል ጉዳዮች ላይ መስማማቱ ታውቋል።
የማንችስተር ሲቲ የረጅም ጊዜ ግብ ጠባቂ ኤደርሰን ሞራዬስ ምንም እንኳን በክለቡ መቆየት እፈልጋለሁ ቢልም፣ ከቱርኩ ክለብ ጋላታሳራይ ጋር ስሙ በስፋት ተያይዞ እየተዘገበ ይገኛል። የ22 አመቱ ጄምስ ትራፎርድ አምና በሻምፒዮንሺፕ በ46 ጨዋታዎች 25 ግቦች ብቻ የተቆጠረበት ሲሆን፣ በበርካታ ጨዋታዎች ግቡን ሳያስደፍር መውጣት ችሏል።
በርንሌይን ወደ እንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ማሳደግ በመቻሉ በእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን እስከመጠራት ደርሷል። ኒውካስትል ዩናይትድ ግብ ጠባቂውን ለማስፈረም ለረጅም ጊዜ ሙከራ ቢያደርግም፣ የተጫዋቹ ፍላጎት የልጅነት ክለቡን ዳግም መቀላቀል ነው ተብሏል።
በ-አልፈሪድ ነስሮ












