እርቅ በሀገር ሽማግሌዎችና በሀይማኖት አባቶች መካከል የሚደረግ ምክክር ሲሆን ፍሬው ጣፋጭ ነው፡፡
የፌደራል መንግስት ችግሮችን በማጣራት በሽምግልና እና በውይይት ለመፍታት ቅድሚያ እንደሚሰጥ በተለያዩ አጋጣሚዎች በተግባር አሳይቷል።
በሀገራችን የረዥም ጊዜ የፖለቲካ ታሪክ እና የአስተዳደር ስርዓት “ብሄራዊ እርቅ፣ ብሄራዊ ምክክር፣ የፖለቲካ ውይይት” ወዘተ … እነዚህን ማህበራዊ ጽንሰ ሃሳቦች በኢትዮጵያ የፖለቲካ ውስጥ በይፋ ያስተዋወቀው ይህ መንግስት ብቻ ነው ቢባል ግልፅ ሃቅ ነው።
“ትርምስ በረከትን ያርቃል” እንደሚባለው ትርምስ ትርምስ ይፈጥራል፣ ግጭት ግጭትን ይፈጥራል እናም በችግር ከባበ ውስጥ እንድንኖር ያደርገናል፤ በረከት ሰላምም ሊያመጣ አይችልም። በታሪካችን ዘላቂ ሰላም በግጭት እና በጦርነት አልመጣም፤ ሊመጣ አይችልም። በአንፃሩ በድርድር፣ በመግባባት እና በሀሳብ ልውውጥ የሚመጣው ሰላም መሰረቱ ጠንካራ ነው፡፡
በዚህ ረገድ ከትግራይ የተውጣጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተወከሉ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ አባላት ጋር ለቀጣይ መድረኮች እድል የሚከፍት
ጥልቅ ውይይት ዛሬ አካሂደናል። በውይይትታችንም በርካታ ጉዳዮች ተነስተው ተመካክረንባቸዋል፡፡ በተለይም የተፈናቃዮች ጉዳይ፣ የትግራይ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚዊ ሁኔታዎች ላይ በዋናነት ምክክር የተደረገባቸው ርዕሰ ጉዳዮች ነበሩ፡፡
በፐብሊክ ዲፕሎማሲው አባላት በኩል በርካታ ሀሳቦች የተነሱ ሲሆን መንግስት ከህዝቡ ጋር ተቀራርቦ መስራት እና ህዝባዊ የውይይት መድረኮችን ማዘጋጀቱን ሊቀጥል ይገባል የሚሉትን ጨምሮ በርካታ ጥያቄዎች ተነስተዋል።
በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት አተገባበር ላይ ያሉ ድክመቶችን እንዴት ማረም እንደሚቻል እና የቃላት አጠቃቀሞችን እንዲሁም አልፎ አልፎ ወደ ግጭት ሊያመሩ የሚችሉ የተሳሳቱ አመለካከቶችን እንዴት ማስተካከል እንደሚቻል እና ትግራይ ከጦርነት ቁስሎች እንድትታከም ብሎም ወደ መደበኛ ህይወት እንድትመለስ በጥልቀት ተወያይተናል።
የትግራይ ተወላጆች እና የትግራይ ምሁራን በሀገራቸው ኢትዮጵያ ፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ውስጥ በስፋት እንዲሳተፉ ሁኔታዎችን መፍጠር በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ካነሳናቸው እና ከተስማማንባቸው ነጥቦች መካከል ይገኙበታል፡፡
የትግራይ ፖለቲካ፣ ጸጥታና ኢኮኖሚ ወደ ቀድሞ ሁኔታው የሚመለስበትን ሁኔታ ለመፍጠር ከህዝቡ፣ ከጊዚያዊ አስተዳደር መንግስት እና ከሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ዝግጁ መሆናችንን አረጋግጠናል።
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ይባርክ!












