ትራምፕ በካናዳ ላይ ከጣሉት 35 በመቶ ታሪፍ በተጨማሪ በሌሎች ሀገራት ላይም ከ 15-20 በመቶ ታሪፍ ለመጣል ማቀዳቸው ተገለጸ፡፡
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ እንዳሰፈሩት ታሪፉ እንደአውሮፓውያኑ ከነሃሴ 1 ቀን ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን እና ካናዳ የአጸፋ እርምጃ ከወሰደች ደግሞ የታሪፍ መጠኑ ከፍ እንደሚል ለካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኔይ ተናግረዋል ።
አሁን ካለበት 25% ወደ 35% የታሪፍ መጠን መጨመሩ የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ከዋሽንግተን ጋር እያደረጉ ያለው የንግድ ስምምነት ንግግር ላይ ተጽዕኖ እንዲፈጥርም አድርጎታል ተብሏል።
የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ሃሙስ ዕለት በኤክስ ገጻቸው ላይ እንዳሰፈሩት መንግስታቸው ከአሜሪካ ጋር በሚያደርገው ንግግር የሀገራቸው የንግድ ድርጅቶች ላይ በሚጣለው ታሪፍ ዙርያ ውይይት ማድረግ እና መሞገታቸውን እንደማያቆሙ አስታውቀዋል፡፡
በአሜሪካ ሜክስኮ- ካናዳ (USMCA) ስምምነት መሰረት በሃይል እና በማዳበሪያ አቅርቦት ላይ የነበረው የ10 በመቶ ታሪፍም ማሻሻያ እንዳልተደረገበት ተጠቅሷል፡፡
ትራምፕ በተለያዩ ሀገራት ላይ የሚያሳልፉት የታሪፍ ጭማሪን በተመለከተም የመጨረሻው ውሳኔ ላይ አልደረሱም ሲል የዘገበው ሮይተርስ ነው፡፡












