በአሜሪካ ከባድ ጥቃት ደርሶባቸዋል ከተባሉት የኢራን ጣቢዎች በአንደኛው ውስጥ የዩራንየም ምርት እንደሚገኝ እና አሁንም ቴህራን ኑክሌር የማበልጸግ አቅም እንዳላት ሀገራቸው እንደምታምን የእስራኤል ባለስልጣን ተናገሩ።
ባለስልጣኑ እንደተናገሩት፣ በኢስፋሃን የሚገኘውን የበለፀገ ዩራኒየም ማግኘት ከባድ እንደሚሆን እና ማንኛውም ሙከራ ደግሞ የእስራኤልን ጥቃት ዳግም እንዲያገረሽ ሊያደርግ እንደሚችል ገልጸዋል።
ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ሰኔ ወር አሜሪካ በሰው አልባ አውሮፕላኖች እና በሚሳኤል በመታገዝ በኢራን ላይ ከፍተኛ ጥቃት እንደፈጸመች እንዲሁም የኢራንን የኑክሌር ተቋማትም ሙሉ በሙሉ እንዳወደሙ በተደጋጋሚ ተናግረዋል፡፡
ማንነታቸውን መግለጽ ያልፈለጉት ከፍተኛ የእስራኤል ባለስልጣን ብዙዎቹ የኢራን የበለፀጉ ዩራኒየሞች በኢስፋሃን የተቀበሩ መሆናቸውን የስለላ መረጃ ያመለክታል ብለዋል። እንደሚታወሰው ኢስፋሃን “ኦፕሬሽን ሚድናይት ሀመር” በተሰኘው ዘመቻ እ.ኤ.አ ሰኔ 22 ቀን በባህር ሰርጓጅ መርከብ በተወነጨፉ ሚሳኤሎች ተመቶ ነበር።
ከፍተኛ ባለስልጣኑ እንደገለጹት እስራኤል የኢራን የኑክሌር መርሃ ግብር ለሁለት ዓመታት ወደ ኋላ ቀርቷል ብላ ገምታለች ያሉ ሲሆን ትራምፕም የኢራን የኑክሌር ተቋማት ሙሉ በሙሉ እንደወደሙ አጥብቀው ይናገራሉ ብለዋል፡፡
የአሜሪካ የስለላ ግምገማዎች ግን ሶስቱም ቦታዎች ፎርዶ፣ ናታንዝ እና ኢስፋሃን ከባድ ጉዳት ቢደርስባቸውም ሙሉ በሙሉ እንዳልወደሙ ደምድሟል። ይህን ሪፖርት የሚደግፉት የእስራኤል ባለስልጣን ኢራን ዳግም የበለፀገ ዩራኒየም መልሳ ማግኘት እንደምትችል አመላክተዋል፡፡
በ ሔርሜላ ተመስገን












