ከ25 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች የሚታደሙበት ሁለተኛው የአፍሪካ አየር ንብረት ጉባኤ እና ሁለተኛው የተመድ የሥርዓተ ምግብ ጉባኤ በጷጉሜን ወር እንደሚካሄድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የውጭ ጉዳይ የሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው፣ የሚኒስቴሩን የበጀት ዓመት አፈጻጸም መነሻ በማድረግ በወቅታዊ ሀገራዊ፣ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።
አምባሳደሩ ከፖለቲካ ዲፕሎማሲ ሥራዎች መካከል ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት በማጠናከር፣ የጋራ ኮሚሽን ስብሰባዎችን በማከናወን እና ሌሎችንም ሀገራዊና ቀጠናዊ ትስስር የሚያጠናክሩ ዲፕሎማሲያዊ ተግባራትን ማከናወን መቻሏን ጠቁመዋል።
በተጨማሪም ከህዳሴው ግድብ ጋር ተያይዞ የግብጽን አመፅ ቀስቃሽነት ለማስቆምና ድርድሩ በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ሳይሆን በአፍሪካ ህብረት እንዲታይ ሆኗል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላትን የህዝብ ለህዝብ ትስስር ለማጠናከር ለ968 የተለያዩ ሀገራት ዜጎች የትምህርት ዕድል መስጠቷንም ተናግረዋል። እንዲሁም ከተለያዩ ሀገራት ጋር የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስከብሩ 11 ስምምነቶች ተፈርመው በፓርላማ መፅደቃቸው አውስተዋል።
ጎረቤት ሀገራትን ባስቀደመ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲና መርህ ጥላ ስር የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ትብብሮችን ለማጠናከር በትኩረት መሰራቱንም አምባሳደር ነብያት ጠቅሰዋል።
አምባሳደር ነብያት ከኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ አንጻር በሰጡት ማብራሪያ፤ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄና በቅርቡ ተግባራዊ የተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ድጋፍ እንዲያገኝ ሰፋፊ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረው፣ ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል ሀገር መሆኗ ተቀባይነትና ተደማጭነቷ ከፍ እንዲል ማድረጉን አውስተዋል።
የተለያዩ መድረኮችን በመጠቀም የኢትዮጵያን ምርቶች፣ የቱሪዝም መዳረሻዎችን እና ሌሎች መሰል ኢኮኖሚያዊ አቅሞችን የማስታወቅ ስራ የተከናወነ ሲሆን፤ በዚህም 806 ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የቅድመ ኢንቨስትመንት ጉብኝት ማከናወናቸውን ገልጸዋል። በበጀት ዓመቱ በ21 ሀገራት በችግር ውስጥ የነበሩ ከ131 ሺህ በላይ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ተደርጓል ነው ያሉት።
የዜጎችን ደህንነትና ክብር የማስጠበቅ ስራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቀዳሚ ኃላፊነት ነው ያሉት ቃል አቀባዩ፤ በተለያዩ ሀገራት የሚኖሩ 1 ሺህ 556 ዜጎች መብታቸው እንዲከበር ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል ሲል የዘገበው ኢ ፕ ድ ነው፡፡












