የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የተጎዱ ዜጎችን የሚያጽናኑ፤ የተሰበሩትን የሚያቃኑ እና የተቸገሩትን የሚረዱ ወጣቶችን መፍጠር የሚያስችል የሰብዓዊነት ትምህርት መሰጠት መጀመሩን የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ አበራ ቶላ ገልጸዋል፡፡

ማኅበሩ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ወጣቱን በሰብዓዊነት ስብዕና የሚያንጽ ሥርዓተ ትምህርት ቀርጾ እያስተማረ ይገኛል ያሉ ሲሆን፣ ሥርዓተ ትምህርቱ 10 የትምህርት አይነቶችን የያዘ ነው፡፡
የስነ-ምግባር፣ የሞራል ግንባታ፣ የሰብዓዊና ሌሎች የትምህርት አይነቶች ተካተዋል ሲሉ የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፣ ፡የትምህርቶች ይዘት በውስጣችን ያለውን ደግነት፣ ርህራሄ፣ ሰው የመርዳት ባህልና ልምዳችንን ይበልጥ የሚያሳድጉ መሆናቸውን በሥርዓተ ትምህርቱም መካተቱት ጠቅሰዋል፡፡
ትምህርቱ የበጎ ፍቃደኞችን ቁጥር ለማሳደግ ከፍተኛ ጥቅም አለው። የበጎ ፍቃደኞች ቁጥርን ለማሳደግም ከስድስት ሰዎች መካከል አንዱ የቀይ መስቀል ማኅበር አባል እንዲሆን የማድረግ ስራ እየተሰራ ነው ሲሉ የማህበሩን እንቅስቃሴ ጠቁመዋል፡፡
አክለውም ዜጎች በተፈጥሮና በሰው ሠራሽ አደጋዎች ከመጎዳቸው በፊት ቀድሞ ለመድረስ የሰብዓዊ ትምህርት ቤት ተከፍቶ የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልዶችን የማፍራት፤ ሰብዓዊነት የተላበሱ ዜጎችን የመፍጠር ስራ እየተሰራ ነው፡፡ ትምህርቶች በማኅበሩ የማስልጠኛ ማዕከል ለወጣቶች እየተሰጡ መሆኑን ፕሬዝዳንቱን ጠቅሶ የዘገበው ኢፕድ ነው፡፡












