
በቻይና ጂልን ነዋሪ የሆነችው የ37 ዓመቷ ቻይናዊት 20 ዓመት ለሚሆን ጊዜ የፊትዋን ሜካፕ አላጸዳሁም ካለች በኋላ መነጋገሪያ ሆናለች።
ጋኦ በመባል የምትታወቀው ቻይናዊት ሴት የፊት ሜካፕን የሚጠቀሙ ሴቶች በአግባቡ መጠቀም እንዳለባችው እና ከተጠቀሙ በኋላም በሚገባ ማጽዳት እንደሚገባ ለማስጠንቀቅ እንዲሁም በእሷ ላይ የተከሰተውን ለማካፈል ወደ ማህበራዊ ሚዲያ ብቅ ብላለች፡፡
ለሀያ አመታት የፊትዋን ሜካፕ እንዳላጸዳች የምትናገረው ወጣቷ በፊትዋ ላይ ከባድ አለርጂ እንዳደረሰባት ትናገራለች። ገና የ15 ዓመት ልጅ ሳለች ነበር እናቷ በምትጠቀምባቸው የፊት መዋብያ ቁሳቁሶች በመጠቀም ሜካፕን መጠቀም የጀመረችው።
ነገር ግን ሜካፕን ከፊት ላይ ማንሳት አድካሚ ስራ በመሆኑ እና ዛሬ አንስተን ነገም መቀባታችን ስለማይቀር በውሃ ብቻ በመታጠብ ቀጣይ ቀን ደግሞ ደርቦ መቀባት ይሻላል በሚል ሀሳብ ላይ በመድረሷ ነበር ለ20 ዓመታት ሳታነሳው የቆየችው፡፡
በቆዳዋ ምክኒያት በየቀኑ እቤት ውስጥ እንደምትደበቅ የገለጸችው ጋኦ ከህክምናዋ በፊት ፊቷ የተሸበሸበ እና የሚያሰቅቅ እንደነበረ አስታውሳለች፡፡ ለዓመታት የብጉር ጠባሳን ብታስተናግድም አሁን ላይ ግን ቆዳዋ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተናግራለች፡፡












