ክረምት አልፎ ብርሃን ሲወጣ በወርሐ መስከረም ዓለም ሁሉ ሊያየው የሚጓጓለት ሠርግ በኢትዮጵያውያን እየተደገሰ ነው።
ይኼ ሠርግ ከዚህ በፊት ዓለም የሚያውቀውን ሠርግ ዓይነት አይደለም። ልዩ የሚያደርገውም ደጋሹ ግለሰብ ሳይሆን ኢትዮጵያ የምትባል ትልቅ እና ታሪካዊት ሀገር፤ ሙሽራውም ሰው ሳይሆን ትሩፋቱ ከኢትዮጵያ አልፎ ለዓለም የሚተርፍ ታላቅ ግድብ መሆኑ ነው።
ኢትዮጵያ ይህንን ታላቅ ሠርግ ስታሰናዳም ለግብዣው የጎረቤት እና የዓባይ ተፋሰስ ሀገራትን በተለይም ግብፅና ሱዳንን በፍጹም ለመታደሙ መጥራትን አልዘነጋችም።
ይልቁኑ በሀገሪቱ መሪ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኩል፣ ለዚያውም በተከበረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፊት ሀገራቱ በዚሁ ታላቅ ድግስ እንዲታደሙ የአክብሮት ግብዣ አቅርባለች።
የመስከረሙ ሙሽራ ኢትዮጵያውያን ያለምንም የብሔር፣ የሃይማኖት፣ የፆታ እና የዕድሜ ልዩነት በጋራ የቆሙለት እና በማህፀን ካለ ጽንስ እና በመቃብር ካለ አስከሬን በስተቀር ሁሉም የአቅሙን ያህል ከተረፈው ሳይሆን ከጉድለቱ አስተዋፅዖ ያደረገበት ታላቁ የዓባይ ግድብ ነው።
አዎን ይህን ታላቅ ግድብ ያለምንም የውጭ ኃይሎች ድጋፍ ኢትዮጵያውያን ለ14 ዓመታት ተንከባክበው፤ የውስጥ እና የውጭ ተግዳሮቶችንም አሸንፈው ለመሞሸር ሽር ጉድ እያሉ ነው።
ክረምቱ አልፎ ጨለማው ሲገፍ እና ብርሃን ሲወጣ ታላቁ የዓባይ ግድብም ለዓለም ሁሉ ብርሃን ሆኖና ተሞሽሮ ይገለጣል።
በዚሁ ጉዳይ ዙሪያ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሰኔ 26 ቀን 2017 ዓ.ም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ማብራሪያ የህዳሴ ግድብ አልቋል እናስመርቀዋለን፤ ከመመረቁ በፊት ብንረብሽ ብለው የሚያስቡ ሰዎች አሉ፤ ነገር ግን ክረምቱ ሲያልቅ እናስመርቀዋለን። ለታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ያለኝ መልዕክት ለግብፅና ለሱዳን ህዳሴ በረከት ነው ሲሉ ገልጸዋል።
የሚመጣው ልማትና ኢነርጂ ለሁሉም ሀገራት የሚተርፍም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በህዳሴ ግድብ ምክንያት የግብፅ አስዋን ግድብ አንድ ሊትር ውሃ እንዳልቀነሰም ሃቁን አስቀምጠዋል።
ኢትዮጵያ እስከበለፀገችና እስካደገች ድረስ የግብፅ እና የሱዳን ወንድሞቻችንን ጉዳት አንፈልግምም ነው ያሉት። ኢነርጂውንና ውሃውን በጋራ እንጠቀማለን፤ ልማትና ዕድገትም ይመጣል ሲሉም አስገንዝበዋል። ኢትዮጵያ ከታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ጋር ለመነጋገር፤ ለመደራደርና፤ ለመሥራት አሁንም ዝግጁ ናት።
ለግብፅና ለሱዳን እንዲሁም ለተፋሰሱ ሀገራት መንግሥታት በሙሉ መስከረም ላይ ህዳሴን ስናስመርቅ የደስታችን ተካፋይ እንዲሆኑ በይፋ እንጋብዛለን ብለዋል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክት በጥቅሉ ሲታይ የታላቁ ዓባይ ግድብ የግንባታ ሥራ በሴራ እንዳልተደናቀፈው ሁሉ ምረቃውንም በባዕዳን ሆነ በባንዳ ማደናቀፍ አይታሰብም የሚል ነው፡፡ የሚያዋጣው ጉዳይም የሠርጉም የትሩፋቱም ተቋዳሽ መሆን እና በጋራ አብሮ መልማት ብቻ ይሆናል፡፡
መረጃው የአማራ በኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ነው












