ሶስተኛውን የአፍሪካ የስራ ዕድል ፈጠራ ፎረም አድዋ ሙዚየም እየተካሄደ ይገኛል።
የእሴት ሰንሰለት መሰረት ያደረገ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ አግሮ-ኢንዱስትሪላይዜሽን ማሳደግ፣ የግብርና እሴት ሰንሰለትን ማዘመን፣ ዲጂታላይዜሽን እና የፋይናንስ አካታችነት ማጎልበትና ማረጋገጥ ፣ የመንግስት እና የግል አጋርነት ማሳደግ፣ የፎረሙ ዋና ትኩረት ጉዳዮች መሆናቸው ተመላክቷል።
በፎረሙ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው የአፍሪካ ሀገራት ከፍተኛ አመራሮች ታድመዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ኢትዮጵያ በዲጂታል ፋይናንስ ላይ ከገጠር እስከ ከተማ መዋለንዋዮን ፈሰስ እያደረገች ትገኛለች ብለዋል። ዓለም በቴክኖሎጂ እየበለፀገች ባለችበት ወቅት የአፍሪካ ሀገራት በህብረት መስራት ይገባናል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ይህንን ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኗን አስገንዝበዋል።

ፎረሙ አፍሪካ ያላትን ወጣት የሰው ሃይል ለልማት በመጠቀም የአፍሪካን ልማትና ህዳሴ ማሳለጥ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ እንደሚመክር የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በመድረኩ ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያን ተግባራዊ ማድረግ ከጀመረች ወዲህ በርካታ የስራ እድሎች የሚፈጥሩበትን ምህዳር ማመቻቸቱን ሚኒስትሯ በመግለፅ ለሶስት ቀናት በሚቆየው ፎረሙ ኢትዮጵያ ከሌሎች አፍሪካ ሀገራት ልምድ ለመለዋወጥ ዝግጁ መሆኗን አብራርተዋል።
አፍሪካ ያላትን እምቅ ሀብት ወደ ተጨባጭ አቅም ለመቀየርና የሥራ አጥነትን ለመቀነስ ፎረሙ ትልቅ ዕድል እንደሚፈጠር ተገልጿል። በዚህም ፎረሙ ላለፉት ሁለት ተከታታይ ዓመታት ሲካሄድ ቆይቷል፡፡
ፎረሙ በሥራ ዕድል ፈጠራ መስክ በአፍሪካ የሚገኙ ፖሊሲ አውጪዎችን፣ ኢንቨስተሮችንና ሥራ ፈጣሪዎችን አህጉራዊ ትስስርና ትብብርን ለማዳበር የሚያስችል ጉልህ ሚናም እንደሚጫወት ተጠቁሟል፡፡
በአህጉሪቱ በስራ እድል ፈጠራ የተያዙ እቅዶች ላይ በመምከርና የተከናወኑ ተግባራትን በመገምገም ቀጣይ አቅጣጫዎች እንደሚቀመጡ ይጠበቃል። ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽንና ከአፍሪካ ኤሌክትሮኒክስ ንግድ ግሩፕ ጋር በመተባበር ያዘጋጀችው ፎረም እስከ ሐምሌ 2 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ ይካሄዳል።
በ-ሀሴት ኃይሉ












