ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገሮች አንጻር ብዙ የተለየች እንደሆነች ብዙዎች በተለያዩ መንገድ ሲገልጿት ይስተዋላል። ከነዚህም ውስጥ ምድረ ቀደምት፣ የ13 ወር ጸጋ፣ የውሃ ማማ፣ የዳቦ ቅርጫት፣ የራሷ ብቻ የሆነ ፊደልና ቀን አቆጣጠር ያላት፣ ወዘተ… በመባል ትገለጻለች፡፡
አንዳንዶቹ አሁን ድረስ በገሃድ የሚታዩ ሲሆን፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ታሪክ ብቻ መስለው ይታያሉ። ከላይ ከተጠቀሱት ነገሮች አንጻር የቀን አቆጣጠር አካል የሆነውን ሰኔ ወር ከሌሎች ወሮች ልዩ የሚያደርጉት ምንድን ናቸው የሚሉትን ለመመልከት እንሞክራልን፡፡
የመጀመሪያው በኢትዮጵያ የሰኔ ወር መገለጫ ሞቃታማ ወራቶች አልፈው የክረምቱ ወቅት መግቢያው ወር ስለሆነ በሁሉም ሰው በኩል በጣም ትኩረት ከሚሰጣቸው ወሮች ውስጥ አንዱ ነው። ፀሐይ እንደ ልብ ስለማትገኝ የቤት እመቤቶች ለክረምት የሚያስፈልጋቸውን የቤት አስቤዛዎች የሚያዘጋጁበት፣ ወንዞች ስለሚሞሉ በገጠር አካባቢ የሚኖሩ ቤተሰቦች ቀድመው የሚጠያየቁበት በመሆኑ ሰኔ ልዩ በታ አለው።
በአርሶ አደሩ በኩል “አንድ ሰኔ የነቀለውን ሁለት ሰኔ አይመልሰውም” በሚል ዝናብ፣ ብርድና ጭቃውን ሳይፈራ የግብርና ስራውን ጠንክሮ ለመስራት በሥነ ልቦና ጭምር ከነቤተሰቡ በበቂ ሁኔታ የሚዘጋጅበት ወር ነው።
መምህራኖችና ተማሪዎች ዓመቱን በሙሉ የደከሙበትን ውጤት የሚያውቁበትና ለሚቀጥለው የትምህርት ዘመን እንዴት እንደሚቀበሉት እራሳቸውን የሚጠይቁበት ነው፡፡
በሌላም በኩል ሰኔ 30 የመንግስት የነባሩ ዓመት በጀት ተመርምሮ የሚዘጋበትና አዲስ በጀት የሚጸድቅበት በመሆኑ፤ የዓመቱ የማህበራዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ስራዎችን ለመስራት አጠቃላይ ሀብት የሚታወቅበት ጊዜ ስለሆነ የሁሉም መነሻ ነው ማለት ይቻላል።
በተጨማሪም በወንዞች ሙላት፣ አርሶ አደሩም ሆነ ሌላው የህብረተሰብ ክፍል በየደረጃው የሚገኙት ፍርድ ቤቶች የሚዘጉበት፣ ከፍተኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ለእረፍት የሚወጣውበት የጊዜ ድልድይ ነው ሰኔ 30 ።
በአጠቃላይ ሰኔ 30 ለኢትዮጵያውያን በሁለንተናዊ መልኩ የነባሩ ዓመት መጨረሻና ለቀጣይ ዓመት ደግሞ መጀመሪያ በመሆኑ በጉልህ ይታወቃል፡፡
በ ሔርሜላ ተመስገን












