የዲዮጎ ጆታ ድንገተኛ ህልፈት አሁንም በእግር ኳስ ቤተሰቡ መነጋገሪያነቱ እንደቀጠለ ይገኛል።
ፖርቱጋላዊው አጥቂ የጋብቻ ስነስርዓትቱን በፈጸመ በሁለተኛው ሳምንት፣የእረፍት ጊዜውን በስፔን በማሳለፍ ላይ እንዳለ ከወንድሙ ጋር በነበሩበት መኪና አደጋ ደርሶ የሁለቱም ህይወት አልፏል። የእግር ኳስ ባላንጣነት፣የዘር ልዩነት ሳይገድበው ሁሉንም የስፖርቱን ቤተሰብ በአንድ ላይ አስተቃቅፎ ሃዘናቸውን እንዲገልጹ አስችሏቸዋል።
በመርሲሳይድ ደርቢ በጽኑ ባላንጣቸውን የሚጠሉት የኤቨርተን ደጋፊዎች ለሊቨርፑሉ ኮከብ በተዘጋጀ ሃዘን መግለጫ ስፍራ የአበባ ጉንጉን ሲያስቀምጡ ታይቷል። የወቅቱ የፕሪምየር ሊጉ ሻምፒዮን ሊቨርፑል በድንገት ላለፈው ኮከብ ክብር ሲል 20 ቁጥር ማልያ ዳግም እንዳይለበስ ውሳኔ አስተላልፏል።
ክለቡ ከዚህም አልፎ በስሩ የሚተዳደሩ የንግድ ተቋማት፣የታዳጊዎች አካዳሚን እና ልዩ ልዩ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ዝግ እንዲሆኑ በማድረግ ሃዘን ተቀምጧል።
በአውሮፓውያኑ 2020 ሊቨርፑልን የተቀላቀለው ዲዬጎ ጆታ በአመታት ውስጥ የሊቨርፑል ውጤት ቀያሪ ተጫዋች መሆኑን አሳይቷል። ቀዮቹ ሽንፈት ሊገጥማቸው በተቃረቡባቸው ጨዋታዎች ባለቀ ድቂቃ ተቀይሮ በመግባት ክለቡን በተደጋጋሚ አድኗል።
አመለ ሸጋ የነበረው ዲዬጎ ጆታ የእግር ኳስ ህይወቱን የጀመረው በሃገሩ ፖርቱጋል በፓኮስ ዴፌራራ ክለብ ነው። ጆታ በፖርቱጋል ሁለተኛ ዲቪዚዮን በሚጫወተው ፓኮስ ባሳየው ተስፋ በ2016 ወደ አትሌቲኮ ማድሪድ መዘዋወር ቢችልም የመሰለፍ ዕድል በማጣቱ ወደ ፖርቱጋሉ ሃያል ክለብ ፖርቶ በውሰት ተጓዘ።
ፖርቶ ተስፈኛውን ወጣት በቋሚ የማስፈረም ዕድሉን መጠቀም ባለመቻሉ ወደ ስፔኑ ክለብ በድጋሚ ቢመለስም፣አሰልጣኝ ዲዬጎ ሲሚዮኔ በድጋሚ በውሰት ውል ወደ እንግሊዝ ሸኙት። በአውሮፓውያኑ 2017 በእንግሊዝ ሻምፒዮንሺፕ ይጫወት የነበረው ዎልቭስ ፖርቱጋላውያን ተጫዋቾችን በወኪሉ ሚኖ ራዮላ አማካኝነት ያሰባስብ የነበረበት ወቅት ነበር።
ሩበን ኒቬሽን ባስፈረሙበት ተመሳሳይ የዝውውር ገበያ ከአትሌቲኮ ማድሪድ ዲዮጎ ጆታን በውሰት ውል ወደ እንግሊዝ እግር ኳስ አመጡት። ወልቭስ በዚያው አመት ወደ ፕሪምየር ሊግ ሲያድግ የጆታ የሜዳ ላይ የሚታይ የማይዋዥቅ አቋም አስተዋጽኦው ከፍተኛ ነበር።
በመጀመሪያ የፕሪምየር ሊግ የውድድር አመታቸውም አስደናቂውን በሁለቱም እግሩ በሚገባ የሚጫወተውን ወጣት በቋሚ ዝውውር በ14 ሚሊዮን ፓውንድ የግላቸው አደረጉት። በፕሪምየር ሊግ ለሁለት የውድድር አመት ታላላቅ ቡድኖችን በመፈተን ክስተተ በነበረው ወልቭስ ከቁልፍ ተጫዋቾች መካከል ጆታ አንዱ በመሆን የብዙ ክለቦች አይን ወስጥ መግባት ቻለ።
በአሰልጣኝ ኑኖ ስፕሪቶ ሳንቶ ቡድን ከሃገሩ ልጆች ከጆአው ሞቲኒሆ እና ሩበን ኒቬሽ ጋር የፈጠረው ጥምረት የጆታን የቡድን ተጫዋችነት እና የጎል ፈጣሪነትን አሳይቷል። በወልቭስ በነበረው ሁለት የውድድር አመት 131 ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ 44 ግቦችን በስሙ አስመዝግቧል።
በአውሮፓውያኑ 2020 የየርገን ክሎፕ ሊቨርፑል 41 ሚሊዮን ፓውንድ ወጪ በማድረግ ተጫዋቹን ያስፈረመው ሲሆን፣ያለፉትን አመስት አመታት ሊቨርፑል ባሳካቸው ዋንጫዎች ተጫዋቹ የማይናቅ ሚና እንደነበረው ቁጥራዊ መረጃዎቹ ይመሰክሩለታል።
ባለፉት ሁለት አመታት ምንም እንኳን በጉዳት ቢፈተንም፣አገግሞ ወደ ሜዳ ሲመለስ ጉልበቱን ሳይሰስት የአንፊልድ ደጋፊን ያስደስት ነበር። በፕሪምየር ሊግ፣ኤፍ ኤካፕ፣ካራባኦ ካፕ በሁሉም ሊባሉ በሚችል የውድድር መስኮች ለቀዮቹ ወሳኝ ግቦችን በማስቆጠር አስፈንጥዟቸዋል። ትላንት ህልፈተ ህይወቱ ኣስኪሰማ ድረስ ለቀዮቹ በተሰለፈባቸው 182 ጨዋታዎች 65 ግቦችን ከመረብ አሳርፏል። ከሂልስ ቦሮው የ96 ደጋፊዎች ሞት አንስቶ ተመሳሳይ የቆየ ሃዘን ያለበት ሊቨርፑል በጆታ አሰቃቂ ህልፈት ሃዘን አጥልቶበታል። አንፊልድ ውድ ልጇን አጥታ ማቅ ለብሳለች።
በ-አልፈሪድ ነስሮ












