በ36ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮኑ ኢትዮጵያ መድን ከሊጉ የወረደውን ስሑል ሽረን ቀን 10 ሰዓት ይገጥማል።

ኢትዮጵያ መድን ከተከታዩ ያለው የነጥብ ልዩነት በመስፋቱ የሊግ አሸናፊነቱን ያረጋገጠው ከአራት ጨዋታ በፊት ነበር።የአሰልጣኝ ገብረመድህን ሃይሌ ቡድን በዓመቱ ወጥ አቋም በማሳየት በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ባለ ድል ሆኗል።
አንጋፋው አሰልጣኝ ገብረመድህን ከሶስት የተለያዩ ክለቦች ጋር የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ባለድል በመሆን ሪከርድ አስመዝግበዋል። ከዚህ ቀደም ከጅማ አባጅፋር እና መቐለ ሰባ እንደርታ ጋር ሻምፒዮን እንደነበሩ ይታወሳል።
መድን የዛሬውን ጨዋታ በድል ከተወጣ ነጥቡን 73 በማድረስ ከተከታዩ ኢትዮጵያ ቡና በ13 ነጥብ ብልጫ ውድድሩን ያጠናቅቃል። ተጋጣሚው ስሑል ሽረ ወደ ብሔራዊ ሊግ መውረዱን ያረጋገጠ ሲሆን፣ካደረጋቸው ያለፉት 6 ጨዋታዎች በሁሉም ተሸንፈዋል።
ፕሪምየር ሊጉን ኢትዮጵያ መድን በ70 ነጥብ ሲመራ፣ኢትዮጵያ ቡና እና ባህርዳር ከተማ በ60 እና 54 ነጥቦች ተከትለውት አጠናቀዋል። ሐዋሳ ከተማ በ53 ነጥብ 4ኛ ደረጃን ይዞ ሲጨርስ፣ የኢትዮጵያ ዋንጫ አሸናፊ እና የቀጣይ ዓመት የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ማጣሪያ ተሳታፊው ሲዳም ቡና 49 ነጥብ ይዞ በ5ኛ ደረጃ ውድድር ዓመቱን ፈጽሟል።
መቐለ ሰባ እንደርታ፣አዳማ ከተማ፣ስሑል ሽረ እና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የተሰናበቱ ቡድኖች ናቸው።
በ-አልፈሪድ ነስሮ












