የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ም/ቤት ምርጫ አስፈፃሚ ቦርድ የ2017 የመጅሊስ ምርጫ ምዝገባን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
የምርጫ አስፈፃሚ ቦርዱ በመግለጫው የመራጮች ምዝገባ ከነገ አርብ ሰኔ 20/2017 ጀምሮ በ315 መስጂዶች እንደሚከናወን የገለፀ ሲሆን መራጮች ለመመዝገብ ሲመጡ በሚመዘገቡበት መስጂድ አካባቢ ነዋሪ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ መታወቂያ ይዘው መምጣት እንደሚጠበቅባቸው አስታውቋል።
ተመራጮች እስከ ምርጫው እለት ድረስ እንደማይታወቁ የተገለፀ ሲሆን ሁሉም ሙስሊም ወደ ምርጫ ጣቢያዎች ሲመጣ ለመምረጥ እንጂ ለመመረጥ እንዳልሆነ ሊታወቅ እንደሚገባ ነው የተገለፀው።
ምርጫው በአምስት ዘርፎች የሚካሄድ መሆኑን የጠቆሙት የምርጫ አስፈፃሚ ቦርድ ሰብሳቢ ጂብሪል ኡስማን ይህም በኡለሞች፣ በምሁራን፣ በወጣቶች፣ በሴቶች እና በሰራተኛ ማህበረሰብ ዘርፍ የሚካሄድ መሆኑን ነው ያስረዱት።
መራጮች ከአምስቱ ዘርፎች መመዝገብ የሚችሉት በአንዱ ዘርፍ ብቻ ሲሆን ተመዝጋቢዎች ቢያንስ እድሜያቸው 18 አመት የሞላው ሊሆን እንደሚገባ ነው የተጠቆመው። ዋና ሰብሳቢው የመራጮች ምዝገባ ለማስጀመር የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን በመግለፅ ቅሬታዎችን ተቀብሎ ማስተካከያ ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል።
የምርጫ ምዝገባው እስከ ሰኔ 29/2017 ድረስ ባሉ የእረፍት ቀናት (አርብ፣ ቅዳሜ እና እሁድ) የሚካሄድ መሆኑም ተጠቁሟል።
በ-አክረም ኑርያ












