
የ2017 ዓ.ም የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ቅንጅታዊ ስራዎችን በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር የሚመክር ሀገር አቀፍ መድረክ ተዘጋጅቷል።
በመድረኩ ላይ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ወጣቶችን ጨምሮ ዜጎች ለማህበረሰባቸው ብሎም ለሀገራቸው በጎ አስተሳሰባቸውን፣ ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውንና እውቀታቸውን የሚያበረክቱበትን ዕድል መፍጠሩን ገልፀዋል።
ተቋማዊ ትብብርና ቅንጅታዊ ሥርዓትን በመዘርጋትና በማጠናከር ረገድ ከፍተኛ የመንግስት ቁርጠኝነት የታየበት መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
አገልግሎቱ መሠጠት ከጀመረበት ጊዜ ወዲህም በስምሪት መስኮችም ሆነ በተሳትፎና ተጠቃሚነት ረገድ በዘርፉ አበረታች ውጤቶች ማስመዝገብ መቻሉን አንስተዋል። የዘንድሮ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የህዝቦችን ትስስርና የአብሮነት እሴቶችን በሚያጠናክሩ ተግባራት እንደሚተገበር ነው የገለጹት።
በክረምት ወራትም ከ31 ሚሊዮን በላይ ወጣቶችንና ሴቶችን በ14 በተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች እንዲሰማሩ በማድረግ ከ52 ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ይሰራል ብለዋል።
በጎ ፈቃደኞች በአረንጓዴ አሻራ፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በትምህርት፣ በጤና አጠባበቅ፣ በስፖርት፣ በኪነ ጥበብ፣ በሰላም ግንባታ፣ የአቅመ ደካሞች ቤት ግንባታና እድሳት፣ በትራፊክ ደህንነት እና ሌሎችም መስኮች በመሠማራት አገልግሎት እንዲሠጡ ለማስቻል መታቀዱን ጠቁመዋል።
እቅዱ ከፌዴራል ጀምሮ በየደረጃው በተደራጀ አግባብ እንደሚተገበር ገልፀው ለስኬታማነቱ ዘርፉን የሚመሩ አካላት በቅንጅት እንዲሰሩ ሚኒስትሯ አሳስበዋል።
በመድረኩ የብልፅግና ፓርቲ አመራሮች፣ የወጣቶችና የሴቶች አደረጃጀቶች፣ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማህበራት፣ የሁሉም ክልልና ከተማ አስተዳደር የወጣቶችና የሴቶች ቢሮዎችና የዘርፍ አመራሮች፣ የፌደራል መንግስት የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል ሲል የዘገበው የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒሰቴር ነው።












