::::::::::::::::::::::::::::::::::::
የመገጭ መስኖ ግድብ ግንባታ የጎንደርንና አካባቢውን ህዝብ በመስኖና የመጠጥ ውሃ ተጠቃሚ የሚያደርገው ነው፡፡ ከአንድ መቶ ሰማንያ ሜትሪክ ኪዩቢክ በላይ ውሃ የሚይዘው የመገጭ ግድብ ፕሮጀክት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ክትትል የሚገነባ ሲሆን የግድቡ ግንባታ አሁን 73.5 በመቶ ላይ መድረሱ የፕሮጀክቱ ግንባታ አማካሪ መሃንዲስ ገልጸዋል።
አጠቃላይ 17 ሺ ሄክታር መሬትን በመስኖ የሚያለማ እንዲሁም ለአካባቢው ነዋሪዎች የንጹህ መጠጥ ውሃን የሚያቀርበው ፕሮጀቱ ላለፉት አስራ ስድስት ዓመታት ሲጓተት የነበረ መሆኑም ለጋዜጠኞች ተገልጿል።

የፕሮጀክቱን ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ በመረዳት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡት መመሪያን ተከትሎ በተጀመረ በአንድ ዓመት ከጥቂት ወራት ውስጥ አሁን ያለበት ጀረጃ ደርሷል ያሉት የጎንደር ከንቲባ ምክትል ከንቲባ ደብሬ የኋላ የፕሮጀክት የማስፈጸም አቅም የታየበት ነው ብለዋል።

በ17 ቢሊዮን ብር በጀት የሚገነባው መገጭ የመስኖ ግድብ በቀጣዩ አመት እንደሚጠናቀቅ በእቅድ ተይዞ በቀን ለሃያ ሰአታት እየተሰራ ይገኛል።
ምክትል ከንቲባዋ ፕሮጀክቱን በቅርበት እየተከታተሉ ለሚገኙት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ምስጋና አቅርበዋል።
የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶችን እያስጎበኘ ነው።
በ-ቆንጂት ዘውዴ












