ኢትዮጵያ በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ስር ያላትን የንግድ ትስስርን ያሳድጋል ተብሎ የታመነበት የኢኮ ትሬድ ፕሮጀክት ማስጀመሪያ መርሀግብር በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።
የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ፕሮጀክቱ ለአራት ዓመታት የሚቆይ መሆኑን በማስጀመሪያ መርሀግብሩ ገልፀዋል። ከአውሮፓ ህብረት በተገኘ 6 ሚሊየን ዩሮ ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ ተግባራዊ እንደሚደረግ ተናግረዋል።
ኢኮ ትሬድ ኢትዮጵያ ተግባራዊ እያደረገች ከምትገኘው የማክሮ ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያ ፣ ከአውሮፓ ህብረት ግሎባል ጌትዌይ እና ከአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 ጋር የተጣጣመ ስለመሆኑ በመድረኩ ተመላክቷል።
የግሉን ዘርፍ አቅም በማጠናከር፣ የንግድ ስምምነቶችን ከየአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና መስፈርቶች ጋር በማጣጣም እና የአህጉራዊ የንግድ ትስስርን ማሳደግ የኢኮትሬድ ፕሮጀክት ዋና አላማ ነው ተብሏል።
በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ትግበራ ውስጥ የአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች እና በሴቶች የሚመሩ ንግዶችን ማበረታታት፣ አህጉራዊ የእሴት ሰንሰለቶችን ለማዋሃድ የንግድ እና የትራንስፖርት መሠረተ ልማቶችን ማሳደግ፣ በተቋማት ውስጥ የንግድ ፖሊሲ እና የምርት ሰንሰለት ልማት አቅም መገንባት ሌላኛዎቹ የፕሮጀክቱ አላማዎች መሆናቸው ተገልጿል።
የኢኮ ትሬድ ፕሮጀክት ኢትዮጵያ በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ውስጥ ያላትን ሙሉ አቅም እንድትጠቀም በማስቻል የኢኮኖሚ እድገቷ እንዲፋጠን ፣ የኑሮ ደረጃ እንዲሻሻል እና ድህነትን በመቀነስ ረገድ ቁልፍ ሚና ይጫወታል ተብሎ ይጠበቃል።
በማስጀመሪያ መርሀግብሩ የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ የአውሮፓ ህብረት ልዑካን፣ የተለያዩ ሀገራት ተወካዮች፣ የግሉ ዘርፍ ባለድርሻ አካላት እና የልማት አጋሮች ተሳትፈዋል።
በ-ሀሴት ኃይሉ












