:::::::::::::::::::::::::::::::::::
የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ህብረት ጋር በመሆን ሁለተኛውን የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ እንደምታስተናግድ አስታውቋል።
ጉባኤው ከጳጉሜን 3 እስከ 5 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚካሄድ የገለፁት የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ “የአረንጓዴ ጉዳይ ውይይቶች አረንጓዴን ማዕከል ያደረጉ እርምጃዎች” በሚል እሳቤ ይደረጋል ብለዋል።
ጉባኤው የአፍሪካን የአየር ንብረት ለውጥ ስትራቴጂን ለመደገፍ ቁልፍ የሆኑ ተፈጥሮ ተኮር መፍትሄዎች ይቀርቡበታል ተብሏል።

ጉባኤው አፍሪካን ድጋሚ አረንጓዴ እንድትለብስ ማድረግ እና የአፍሪካን አጋርነት ማጠናከር ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑን ሚኒስትሯ አመላክተዋል።
ኢትዮጵያ የአየር ብክለትን ለመከላከል በርካታ አመራጮችን እየተጠቀመች መሆኑን ያነሱቱ ሚኒስትሯ በተለይም ለተከታታይ አመታት ተግባራዊ ያደረገችው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ያበረከተው አስተዋጽኦ የላቀ ነው ብለዋል።
ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እየተደረገ ያለው ቅድመ ዝግጅት ሀገሪቱ የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ የተለያዩ ሀገራት እና የአለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸውን እንግዶች ተቀብላ ለማስተናገድ ተዘጋጅታለች ብለዋል፡፡
በ-ሀሴት ኃይሉ












