::::::::::::::::::::::::::
የቀድሞው የቶተንሃም ሆትስፐር እና ሪያል ማድሪድ ኮከብ ጋሬዝ ቤል፣ በእንግሊዝ የሊግ እርከን ሁለተኛ በሆነው ቻምፒዮንሺፕ በዘንድሮው አመት በወረደው ፕሊመዝ የባለቤትነት ድርሻ መግዛቱ ተዘግቧል።
የፕሊመዝ አርጋይል አሜሪካዊው ባለቤት ሳይመን ሃሌት ከወራት በፊት የክለቡን ከፊል ባለቤትነት መሸጥ እንደሚፈልጉ ተናግረው ነበር።
ዌልሳዊው ቤል እንደ ቀድሞ የቡድን አጋሩ ሞድሪች ሁሉ በእንግሊዝ የክለብ ከፊል ባለቤትነትን መግዛት ችሏል።
በቶተንሃም እና ሪያል ማድሪድ አብሮት የተጫወተው ሉካ ሞድሪች ከወራት በፊት በስዋንሲ ሲቲ የባለቤትነት ድርሻ መግዛቱ ይታወሳል።
ቤል በክለቡ ከፊል ባለቤትነት መግዛቱ እንጂ፣ምን ያህል ድርሻ እንደሆነ እስከሁን የታወቀ ነገር የለም።
ፕሊመዝ አርጋይል በቀጣይ አመት በእንግሊዝ ሶስተኛው የሊግ እርከን (ሊግ 1) የሚወዳደር ሲሆን የቀድሞውን የማንችስተር ዩናይትድ ተጫዋች ቶም ክሌቨርሊን በዋና አሰልጣኝነት ሾሟል።
በ-አልፈሪድ ነስሮ












