::::::::::::::::::::::::::::
በደቡብ አፍሪካ በደረሰ የጎርፍ አደጋ 49 ሰዎች መሞታቸውን የአካባቢው ባለስልጣናት አስታወቁ፡፡
የጎርፍ አደጋው የተከሰተው በአገሪቷ በደቡብ ምስራቅ ክፍል ከፍተኛ ዝናብ ፣ ኃይለኛ ንፋስ እና እንዲሁም በአንዳንድ አካባቢዎች በረዶ ካመጣ በኋላ በምስራቃዊ ኬፕ አውራጃ አካባቢ ነው፡፡
በጎርፍ አደጋው የሞቱ ሰዎች ቁጥር 49 መድረሱን የገለፁት የአካባቢው ባለስልጣናት በርካቶችም ስለመጥፋታቸው ጠቁመው የጠፉ ሰዎችን የማፈላለግ ስራው ተጠናክሮ መቀጠሉንም አመላክተዋል፡፡
በምስራቃዊ ኬፕ መሪ የሆኑት ኦስካር ማቡያኔ ለጋዜጠኞች በሰጡት መማብራሪያ ከአየር ንብረት ጋር የተያያዘ በግዛቷ ካጋጠሙ በጣም አስከፊ አደጋዎች መካከል አንዱ ነው ብለዋል፡፡
የጠፉትን ሰዎች በመፈለግ ላይ ነን አሁንም ግን አዳዲስ አስክሬኖች እያገኘን ነው ብለዋል፡:በአደጋው በርካታ ቤቶች የፈረሱ ሲሆን በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤተሰቦች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በጊዜያዊ ማእከላት ተጠልለዋል ቢያንስ 58 ትምህርት ቤቶች እና 20 ሆስፒታሎች ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡
የአካባቢው መሪ ለሟቾቹ ቤተሰቦች የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን በድጋሚ እንገልፃለን እናም ነዋሪዎች ነቅተው እንዲጠብቁ እና የአካባቢውን የአደጋ አስተዳደር ቡድኖች መመሪያ እንዲከተሉ
አሳስበዋል፡፡
በሄርሜላ ፍቃደ












