:::::::::::::::::::::::::
የጋዛ የባህር ላይ እገዳን ጥሶ ሊገባ የሞከር የእርዳታ መርከብ፣ የአየር ንብረት ተሟጋቿን ግሬታ ቱንበርግን እና ሌሎች ታዋቂ ሰዎችን ጭኖ ሲጎዝ የነበረው መርከብ ፣ በሰኞ እለት መባቻ ላይ በእስራኤል ኃይሎች ተይዞ ወደ እስራኤሉ የአሽዶድ ወደብ እንዲያመራ ተደርጓል።
“ማድሊን” የተሰኘውና በፍሪደም ፍሎቲላ ኮአሊሽን የሚተዳደረው ይህ መርከብ፣ ለጋዛ ሰብአዊ እርዳታ ለመስጠት እና እየተካሄደ ስላለው ሰብአዊ ቀውስ ግንዛቤ ለመፍጠር ከሲሲሊ ተነስቶ ነበር። በመርከቡ ውስጥ ከ12 በላይ አክቲቪስቶች እንደነበሩ ተዘግቧል፤ ከእነዚህም መካከል “ጌም ኦፍ ትሮንስ” የተሰኘው ፊልም ተዋናይ ሊያም ከኒንግሃም እና የፈረንሳይ የአውሮፓ ፓርላማ አባል ሪማ ሀሰን ይገኙበታል።
ከመያዛቸው በፊት የተቀረጹ የአክቲቪስቶች ቪዲዮ መልዕክቶችን ይፋ አድርጓል፤ ከእነዚህም መካከል ቱንበርግ “ይህን ቪዲዮ ካያችሁት፣ በእስራኤል ወራሪ ኃይሎች ወይም እስራኤልን በሚደግፉ ኃይሎች ታፍነናል” ስትል ተናግራለች። ደጋፊዎቿም የእስራኤል መንግስትን እንዲለቃቸው እንዲጠይቁ አሳስባለች።
በተቃራኒው፣ የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መርከቡ “በሰላም ወደ እስራኤል የባህር ዳርቻ እየደረሰ ነው” ሲል አረጋግጧል፤ ተሳፋሪዎቹም “ወደ ትውልድ አገራቸው እንደሚመለሱ ይጠበቃል” ብሏል። ሚኒስቴሩ ዓላማው ዝናን ማግኘት እንደሆነ ገልጸው ፤ የተጫነውም የእርዳታ መጠን “ከአንድ የጭነት መኪና ያነሰ” መሆኑን ጠቅሷል። በመርከቡ ላይ ያለው ማንኛውም እርዳታ “ትክክለኛ በሆኑ ሰብአዊ እርዳታ ማስተላለፊያ መንገዶች” አማካኝነት ወደ ጋዛ እንደሚተላለፍም አክሏል።
የእስራኤል የመከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትስ ቀደም ሲል ለፍሎቲላው ጠንካራ ማስጠንቀቂያ ሰጥተው ነበር፤ የእስራኤል መከላከያ ሰራዊት (IDF) ወደ ጋዛ እንዳይደርስ እንዲያግደው መመሪያ ሰጥተው፣ ተልዕኮውንም “የህዝብ ትኩረት ለማግኘት የሚደረግ ጥረት” በማለት ገልጸውታል። በተጨማሪም አክቲቪስቶቹ እንደደረሱ የጥቅምት 7ቱን የሀማስ ጥቃቶች ቀረጻዎች እንደሚታዩ አስታውቀዋል።
ይህ ክስተት በእስራኤል የባህር ላይ የጋዛ እገዳ ዙሪያ ያለውን ቀጣይ ውጥረት ያሳያል፤ እስራኤል ይህ እገዳ ለደህንነቷ ወሳኝ እንደሆነና የጦር መሳሪያዎች ወደ ሀማስ እንዳይደርሱ ለመከላከል እንደሆነ ትገልጻለች። ሰብአዊ እርዳታ ድርጅቶችና አክቲቪስቶች ግን በእገዳው ምክንያት በአካባቢው ያለውን ከባድ ሰብአዊ ፍላጎት በመጥቀስ፣ እገዳው እንዲነሳ ጥሪያቸውን ማሰማታቸውን ቀጥለዋል።
በ- ሃና ተሰማ












