June 2, 2025
ለ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቋል። የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላትወርቅ ኃይሉ በ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ቅድመ ዝግጅትና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። ቦርዱ ከሕግ ማሻሻያ ጥናት ጀምሮ በቴክኖሎጂ ፣ በሰው ኃይል ፣ በአቅም ግንባታ እና በአስፈላጊ ቁሳቁሶች ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን ዋና ሰብሳቢዋ ገልፀዋል።

ምርጫን የተመለከተው አዋጅ ጋር በተያያዘም የማሻሻያ ጥናት ተደርጎ ለሚመለከተው አካል መቅረቡንም ያስታወሱት ወ/ሮ ሜላትወርቅ፣ ከአቅም ግንባታ ጋር በተያያዘ ስለ ምርጫ አጠቃላይ ኦፕሬሽንና የቦርዱን ተቋማዊ ብቃት ለማሳደግ የሚረዳ የምርጫ ኦፕሬሽናል ማንዋል ማዘጋጀታቸውን ተናግረዋል ።
የምርጫ አስፈፃሚዎች ምልመላ በኦንላይን ፈተና ወስደው እንዲሆን ለማድረግ አዲስ የሶፍትዌር ሲስተም አበልፅገናል። የቅርንጫፍ ጽ/ቤቶችን አቅም የማደራጀት ስራ በተመለከተ በተደጋጋሚ ስልጠና በመስጠት ብቁ ለማድረግ መሰራቱንም ሰብሳቢዋ ያነሱት።
የዕጩዎች ምዝገባን የሚያቀላጥፍ ሶፍትዌር፤ እንዲሁም የሎጀስቲክስ እቃዎች ትራኪንግ ሲስተም በማበልፀግ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል። በቀጣይ በሚወጣ የጊዜ መርሐ-ግብር መሰረት የዕጩዎች ምዝገባ እና የመራጮች ምዝገባ ለማከናወን የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት መደረጉንም አስረድተዋል።













