የምዘና ውጤቱ በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ 15ኛ ሆኖ ላጠናቀቀው ክለቡ ሌላ አሳፋሪ አሀዝ ሆኖ ተመዝግቧል።
ዘ አትሌቲክ እንደዘገበው፣ በእግር ኳስ ክለቡ ያለው የደረጃ ዝቅጠት ከሜዳ ውጪም አለ።
በኦልድትራፎርድ ስታዲየም አይጦች በበርካታ የመስተንግዶ አካባቢዎች ከተገኙ በኋላ ክለቡ ከአምስቱ የሁለት ኮከብ የምግብ ንፅህና ደረጃ እንደተሰጠው ይፋ ሆኗል።
የጤና ተቆጣጣሪዎች ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ አምባሳደር ላውንጅ፣ ቁጥር 7 ስዊት እና የዲያብሎስ ባርን ጨምሮ በሰባት የተለያዩ የስታዲየሙ ክፍሎች በርካታ አይጦች አሉ።
በወጥ ቤቶቹ ውስጥና ምግብ በሚዘጋጅባቸው ቦታዎች ላይም በተመሳሳይ አይጦች መታየታቸውን ሪፖርቱ አስረድቷል።
ከሚመከረው ቀን በላይ ክፍት ሆነው የቆዩ የቅመማ ቅመም ኮንቴይነሮች መኖራቸውንና በተለያዩ የስታዲየሙ ክፍሎች የፍል ውሃ እና የሳሙና እጥረት መከሰቱም ተመላክቷል።
በመስተንግዶ አካባቢዎች ያለው አጠቃላይ ንፅህና በተቆጣጣሪዎቹ ከደረጃ በታች ተብሏል።
የማንቸስተር ዩናይትድ ቃል አቀባይ አለን ኪጋን በበኩላቸው፣ በመላው ኦልድትራፎርድ ጠንካራ የተባይ መቆጣጠሪያ ዘዴን ተግባራዊ እያደረጉ እንደሚገኙ አስገንዝበዋል።
በሁሉም የምግብ ማቅረቢያ ቦታዎች በርካታ ሳምንታዊ ፍተሻዎች መደረጋቸውን በማስታወስ ንፅህናቸው ከፍተኛ መሆኑን ለማረጋገጥ ጥብቅ እርምጃዎችን እንደሚወስዱ ቃል ገብተዋል።
ክለቡ በንፅህና ደረጃው ላይ ችግር ሲያጋጥመው ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ባለፈው የውድድር ዘመን በ2023 ጥሬ ዶሮን ለተወሰኑ እንግዶች ካቀረበ በኋላ ከአምስት አንድ ኮኮብ እንደተሰጠው ይታወሳል።
በ-ይበልጣል ሰውነት












