:::::::::::::::::::::::::::::::::
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ 25ኛውን የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከል፣ ጉራራ ቅርንጫፍ መርቀው ስራ አስጀምረዋል።
ከንቲባዋ በአዲሱ ማዕከል የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ ለአቅመ ደካሞችና ለተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች ለተጋለጡ ወገኖች ማዕድ አጋርተዋል።

ከንቲባ አዳነች በዚሁ ወቅት፥ የከተማ አስተዳደሩ ከግሉ ዘርፍ ጋር በመተባበር የምገባ ማዕከላትን በማስፋፋት በቀን አንድ ጊዜ መብላት የማይችሉ ወገኖችን እየመገበ መሆኑን ተናግረዋል።
ዛሬም የከተማ አስተዳደሩ 25ኛውን የምገባ ማዕከል በየካ ክፍለ ከተማ ፈረንሳይ ጉራራ አካባቢ መከፈቱን ተናግረዋል።
ማዕከሉ በአያት አክሲዮን ማህበር ድጋፍ መገንባቱን ጠቅሰው፤ ድርጅቱ በማዕከሉ አቅመ ደካማ ወገኖችን የሚመግብ በመሆኑም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
መስጠት አያጎድልም፤ መለገስም በረከት ነው ያሉት ከንቲባዋ፤ በቀጣይም ባለሀብቶች ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።












