፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡
የኢትዮጵያን የግብርና እና ምግብ ሥርዓት ለመለወጥ የሚያስችል ትብብርን ለማጠናከር ያለመ ውይይት፤ በገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው እና በዓለም ምግብ ድርጅት የአግሪፉድ ኢኮኖሚክስ ዳይሬክተር ዶ/ር ዴቪድ ላቦርዴ መካከል ተደርጓል።
ውይይቱ ያተኮረው የኢትዮጵያ ምግብ ነክ የግብርና ምርቶች ሂደትን፣ ስርጭትን እና ፍጆታን በተመለከተ የኢትዮጵያን ብሔራዊ የምግብ ስርዓት ስትራቴጂ ከዓለም ምግብ ድርጅት ፍኖተ ካርታ ጋር በማጣጣም ላይ ነውም ተብሏል።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው በውይይቱ ላይ ኢትዮጵያ በዓለም ምግብ ድርጅት የዓለም ፍኖተ ካርታ መሰረት ከአምስቱ ፓይለት ሀገራት አንዷ ሆና መመረጧ ያለውን ጠቀሜታ አፅንዖት ሰጥተዋል።

አክለውም ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለችው ዘርፉን የማሻሻል እንቅስቃሴ እንድታጠናክር እንዲሁም፤ በቴክኒክ እውቀትና በዓለምአቀፍ ልምድ ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር የተሻለ ትብብር እንድታደርግ ትልቅ እድል እንደሚፈጥር አመልክተዋል።
ዶ/ር ላቦርዴ በበኩላቸው የዓለም ምግብ ድርጅት ኢትዮጵያን በዚህ የለውጥ ጉዞ ለመደገፍ ያለውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል።
ሀገሪቱ በምግብ ሥርዓቱ ውስጥ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የጀመረችውን ንቁ አካሄድ አድንቀው፤ በቀጠናው ላሉ ሌሎች ሀገራት ተምሳሌት ለመሆን አቅም እንዳላትም ማንሳታቸውን የኢቢሲ ዘገባ ያመለክታል።












