
የኢራኑ ከፍተኛ መሪ አያቶላ አሊ ካሜኒApril 12, 2025
ቶማይ መኮንን
የኢራን እና አሜሪካ ልዑካን የመጀመሪያውን የኔክሌር ውይይት ለማድረግ ኦማን መግባታቸው ተገለጸ፡፡ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናል ትራምፕ ዳግም ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ የኑክሌር መርሀ-ግብሯን እያስፋፋች የምትገኘው ቴህራን፣ ከዋሽንግተን ጋር በኑክሌር ጉዳይ ልትመክር ነው፡፡
ምንም እንኳ ለግማሽ ክፍለ ዘመን በጠላትነት የኖሩት ሁለቱ ሀገራት በኑክሌር ጉዳይ ላይ ከስምምነት ለመድረስ አስቸጋሪ ቢሆንባቸውም ወደ ድርድር መምጣታቸው ግን መልካም ጅምር ነው ተብሏል፡፡ ዶናልድ ትራምፕ፣ ኢራን የኑክሌር መርሀ-ግብሯን የማስፋፋት ዘመቻዋን የማታቆም ከሆነ አሜሪካ የአየር ጥቃት እንደምትፈጽም መዛታቸው ይታወሳል፡፡
ኢራን በበኩሏ የአሜሪካ ማስፈራሪያ ከምንም ነገር እንደማያስቀራትና የትኛውንም ጫና እንደማትቀበል ስትናገር ቆይታለች፡፡ በመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት ውዝግብ ውስጥ የሚገኙት ቴህራን እና ዋሽንግተን የኑክሌር ፍጥጫውን ለማርገብ ይመስላል ዛሬ ኦማን ላይ የሚገናኙት፡፡ በአሜሪካ በኩል የመካከለኛው ምስራቅ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ ከፑቲን ጋር ከተወያዩ በኋላ በቀጥታ ወደ ኦማን አምርተዋል፡፡
በሌላ በኩል የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቼ ከኦማኑ አቻቸው ባዳር አል ባሶይድ ጋር እንደተገናኙም ታውቋል፡፡ አልጀዚራ እና ኤቢሲ ኒውስ ዘግበውታል፡፡












