ማንችስተር ዩናይትድ ትላንት ምሽት በዩሮፓ ሊግ ወደ ፈረንሳይ አቅንቶ ከሊዮን 2-2 በተለያየበት ጨዋታ ግብ ጠባቂው አንድሬ ኦናና ውድ ዋጋ ያስከፈለ ስህተት ሰርቷል።
ካሜሮናዊው ግብ ጠባቂ በያዝነው የውድድር አመት በተለያዩ ጨዋታዎች 8 የጎላ ስህተት የፈጸመ ሲሆን በፕሪምየር ሊጉ ከየትኛውም ግብ ጠባቂ በላይ ቀዳሚ ያደርገዋል።
ከምሽቱ ጨዋታ አስቀድሞም በቀድሞው የቀያይ ሰይጣኖቹ ተጫዋች ኒማኒያ ማቲች “በዩናይትድ ታሪክ ደካማው ግብ ጠባቂ” ተብሎም ነበር።
አሰልጣኝ ሩበን አሞሪም ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በሰጡት አስተያየት “ እኔ በአሰልጣኝነቴ ከመጣሁ ጊዜ አንስቶ ከኦናና በላይ ስህተት ሰርቻለሁ” በማለት ስላቅ እና ማንጓጠጥ እየደርሰበት ያለውን ተጫዋች ተከላክለዋል።
አክለውም በግብ ጠባቂው ላይ አሁንም ሙሉ መተማመን እንዳለቸው ተናግረዋል።
አሰልጣኙ ይህንን ይበሉ እንጂ ለክለቡ ቅርበት ያላቸው ዘጋቢዎች እንደሚሉት ዩናይትድ በክረምት በስፍራው ላይ አማራጭ ማጤኑ አይቀርም።
በ- አልፈሪድ ነስሮ












