፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡
የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር የንግድ ዘርፉ የሚመራበትን ረቂቅ ፖሊስን በማዘጋጀት ከንግዱ ማህበረሰብ፣ ከምርምር ተቋማት፣ ከንግድ ዘርፍ ማህበራት ጋር ምክክር እያካሄደ ይገኛል።
የንግድ ዘርፉ የሚመራበት ራሱን የቻለ ፖሊሲ ባለመኖሩ የገቢ ንግዱ ወጥ በሆነ እሳቤ እና አደረጃጀት እንዳይመራ ማነቆ ሆኖበታል ሲሉ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በመድረኩ ተናግረዋል።
ሚኒስትሩ የወጪ ንግዱ ፍትሃዊ ውድድር የሚጎድለው፣ የተለያዩ ህገ-ወጥነትና ብልሹ አሰራሮች የበዙበት፤ ሸማቾችን ያማረረ የግብይት ሁኔታዎች የሚስተዋሉበት እና በአለም አቀፍ ገበያም ተወዳዳሪነትን ያላረጋገጠ ዘርፍ ነው ብለዋል።

በንግድ ዘርፉ የሚስተዋለውን ክፍተቶች ለመቅረፍ የንግድ ዘርፉን ለማዘመንና ተወዳዳሪ ለማድረግ እንዲሁም ሁሉም የንግድ ዘርፎች ተጠቃሚ የሚያደርግ የንግድ ፖሊሲ ማስፈለጉን ሚኒስትሩ አንስተው ባለፉት ዓመታት በተለያዩ አካላት ፖሊሲው ሲገመገም እና ማሻሻያዎች ሲደረግበት መቆየቱን አመላክተዋል።
ይህ ረቂቅ ፖሊሲ በንግዱ ዘርፍ የሚስተዋለውን ዘርፈ ብዙ ማነቆዎች የሚፈታ፣ ቀልጣፋና ፍትሀዊነት የሰፈነበት የሀገር ውስጥ የንግድ ስርአትን የሚፈጥር ነው ተብሏል።

ግልፅና ፍትሀዊ የገቢና ወጪ ንግድ አስተዳዳር ማዕቀፍ መዘርጋት የሚያስችል ነው የተባለለት ረቂቅ ፖሊሲው ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የምርት ትስስር ውስጥ እንድትሳተፍ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት በመድረኩ ተመላክቷል።
የንግድ ፖሊሲ ሀገራዊ የብልፅግና ራዕይ ለማሳካት ጉልህ ሚና ያለውን የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የአስር ዓመቱን የልማት ዕቅድ እና የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎች መነሻ በማድረግ መዘጋጀቱ ተገልጿል።
በ-ሀሴት ኃይሉ












