ዶናልድ ትራምፕ ይፉ ያደረጉትን አዲሱን የታሪፍ ጭማሪ ውሳኔ ተከትሎ የበርካታ ሀገራት መሪዎች ተቃውሟቸውን እያሰሙ ይገኛሉ።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሁሉም የንግድ አጋሮቻቸው ላይ በትንሹ ከ10 እስከ 50 በመቶ የታሪፍ ጭማሪ አድርገዋል።
አዲሱ የታሪፍ ጭማሪ ወደ አሜሪካ ምርቶቻቸውን የሚልኩ 100 ሀገራት ላይ ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን፣ የተመረጡ 60 ሀገራት ላይ ከፍተኛ የታሪፍ ጭማሪ ይደረጋል።
የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት ከፍተኛ የታሪፍ ጭማሪ ከተደረገባቸው ሀገራት መካለል ይገኛሉ።
ይህንን የትራምፕ ውሳኔ ተከትሎ የጣሊያኗ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ በአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት ላይ የተጣለው የ20 በመቶ የታሪፍ ጭማሪ ፍፁም የተሳሳተ ውሳኔ ነው፤ ለአውሮፓም ሆነ ለአሜሪካ አይበጅም ብለዋል።

የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት በበኩላቸው “የአለም የንግድ ጦርነት አሁን ተጀምሯል፤ ይህንን ቀውስ ለመጋፈጥ መንግስታችን ሁሉንም አቅሙን ይጠቀማል” ብለዋል።
የአውስትራሊያ መሪ አንቶኒ አልባኒዝ እንዲሁ በአሜሪካ የተጣለብን የ10 በመቶ የታሪፍ ጭማሪ “አግባብነት”የሌለው ነው በማለት የትራምፕን ውሳኔ አጣጥለውታል።
የስፔን ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የስዊዝ ፕሬዝዳንት ፣ የአይሪሽ ጠቅላይ ሚኒስትር ፣ የኮሎምቢያና የብራዚል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ ኒውዚላንድ የንግድ ሚኒስትርና ሌሎችም የትራምፕ ውሳኔ ላይ ተቃውሟቸውን ከገለፁ ውስጥ ይጠቀሳሉ።
ዘገባው የሮይተርስ ነው።
በ-የአብስራ ሚሊዮን











