አሰልጣኝ ሩበን አሞሪም ብሩኖ ፈርናንዴዝ የትም አይሄድም አሉ
:::::::::::::::::::::::::::::::::::::::
የማንችስተር ዩናይትድ አምበል ከሰሞኑ ስሙ ከስፔኑ ክለብ ሪያል ማድሪድ ጋር ጠንከር ብሎ ሲያያዝ ሰንብቷል።
የ30 አመቱ ፖርቱጋላዊ ምንም እንኳን ከቀያዮቹ ሰይጣናት ጋር እስከ 2027 የሚያቆይ ኮንትራት ቢኖረውም ትልቅ ዋንጫ የማሳካት ህልሙን ለማሳካት የሎስብላንኮቹን ጥያቄ ያጤነዋል ተብሏል።
ዛሬ ምሽት በፕሪምየር ሊጉ ማንችስተር ዩናይትድ ከኖቲንግሃም ፎረስት የሚደረገውን ጨዋታ አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት አሰልጣኝ ሩበን አሞሪም ፈርናንዴዝን በተመለከተ “የትም አይሄድም” ሲሉ ተደምጠዋል።
ከተጫዋቹ ጋር መነጋገራቸውን የገለጹት አሰልጣኙ “ሊፈጸም የማይችል” ዝውውር ብለውታል።
በማንችስተር ዩናይትድ ያለፉትን አመታት በማይዋዥቅ አቋም በማገልገል የሚገኘው ፈርናንዴዝ በክለቡ የተዳከመ ውጤት ሳቢያ ተገቢውን ሙገሳ አላገኘም ይባላል።
ተጫዋቹ በዘንድሮው አመት በሁሉም ውድድሮች እስካሁን 16 ግቦችን በማስቆጠር የክለቡ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ነው።
ጎል በማስቆጠር እና የመጨረሻ ኳስ ለቡድን አጋሮቹ በማድረስ የሚበለጠውም በሞሃመድ ሳላህ እና በ እርሊንግ ሃላንድ ብቻ ነው።
ማንችስተር ዩናይትድ 13ተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ አስቸጋሪ የውድድር እያሳለፈ ሲሆን ዛሬ ምሽት 3፡45 ከሜዳው ውጪ በማቅናት 3ተኛ ስፍራ ከሚገኘው ኖቲንግሃም ፎረስት ይጫወታል።
በ – አልፈሪድ ነስሮ












