።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።
በሃዋሳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ውስጥ የሚገኘው የጃፓኑ የሶላር አምራች ኩባንያ ቶዮ ሶላር በ47 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ተጨማሪ የማስፋፊያ ስራዎችን ለማከናወን ማቀዱን አስታወቀ፡፡
ኩባንያው ለማስፋፊያ ስራው 28 ሺህ ካሬ ሜትር መሬት እንደሚረከብም ተገልጿል።
ዮዮ ሶላር በልዩ የኢኮኖሚ ዞኑ ውስጥ የሚገኘውን በመጀመሪያ ምዕራፍ በ60 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር የተገነባውን ፋብሪካው ስራ ለማስጀመር ዝግጅት እያደረገ ይገኛል።
ይህም ኩባንያው በኢትዮጵያ ያለውን አጠቃላይ ኢንቨስትመንት ወደ 110 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ከፍ እንደሚያደርገው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን መረጃ ያመለክታል።

የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ እና ሊቀመንበር ጁንሴይ ሪዩ ለሶላር ሴል ምርቶች ያለው ዓለም አቀፋዊ ፍላጎት እና ትዕዛዝ በመጨመሩ ምክንያት በኢትዮጵያ ተጨማሪ የማስፋፊያ ስራ ማከናወን እና ተደራሽን ማስፋት አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ገልጸዋል።
ኩባንያው በሃዋሳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ውስጥ ተጨማሪ 28 ሺህ ካሬ ሜትር ስኩዌር ቦታ እንደሚረከብ ተነግሯል።
የማስፋፊያ ስራ በፍጥነት እያደገ ላለው የኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል ኢንዱስትሪ ማዕከል በመሆን እንደሚያግዝ ያስታወቀው ኮርፖሬሽኑ ግንባታው በሐምሌ ወር በማጠናቀቅ የምርት ሂደቱን በነሐሴ ወር ለማስጀመር እቅድ መያዙን ገልጿል።
ኩባንያው በህዳር ወር 2017 ዓ.ም የተፈራረመው የ150 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የፀሐይ ኃይል አቅርቦት ስምምነት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የታዳሽ ኃይል አቅርቦት ገበያ ላይ ወሳኝ ተዋናይ እንድትሆን ያስችላታል የሚል እምነት ተጥሎበታል። ዘገባው የኢዜአ ነው