፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ህዳር 19 2017| NBC ETHIOPIA -አለም አቀፍ የጸረ- ጾታዊ ጥቃት ቀናት ዘንድሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ33ኛ ጊዜ “UNITE to End Violence against women and Girls”፤ በሀገራችን ደግሞ ለ19ኛ ጊዜ “የሴቷ ጥቃት የእኔም ነው ዝም አልልም” በሚል መሪ ቃል ከህዳር 16 ጀምሮ እስከ ታህሳስ 1 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ ለ16 ተከታታይ ቀናት እየተከበረ ይገኛል።
በዘመቻው እያንዳንዱ ቀናት የራሳቸው የድርጊት መርሃ ግብር ተዘጋጅቶላቸው የሚከበሩ ሲሆን፣ በእነዚህ ቀናት ወንዶች የፀረ ጾታዊ ጥቃት ዘመቻ አጋር እንደሆኑ ለማሳየት ነጭ ሪባን ያስራሉ፣ ሴቶቹ ደግሞ ብርቱካናማ ቀለም ያለው ሪባን ያስራሉ፡፡በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት ጾታ የማይለይ ሁሉንም የሚመለከት ማኅበራዊ ችግር መሆኑን የሚያመላክት ነው፡፡
በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት ይቁም የሚለው ዘመቻ መነሻ የተፈጸመው እ.ኤ.አ. በዲሴምበር 6 ቀን 1989 በአገረ ካናዳ በሞንትሪያል ኩቤክ ከተማ በኢኮል ፓሊ ቴክኒክ ዩኒቨርሲቲ በተፈጸመ ግድያ ነው፡፡ ማርክ ሊፓይን የተባለ የ25 ዓመት ወጣት በዕለቱ 11 ሰዓት አካባቢ የሞንቲሪያል ዩኒቨርሲቲ አካል ወደሆነው የኢንጂነሪንግ ኮሌጅ ይገባል፡፡ ኮሌጁን በሚገባ የሚያውቀው ሊፓይን ወደ ሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ትምህርት ክፍል ያመራል፡፡ 50 ተማሪዎች ካሉበት በሁለተኛው ፎቅ ከሚገኘው አንዱ ክፍል ይገባና ሁሉም እንዲያዳምጡት ይጠይቃቸዋል፡፡ ተማሪዎቹም ንግግሩ የቀልድ መስሏቸው ቸል ሲሉት በቦርሳው የያዛትን ሽጉጥ በማውጣት ወደ ጣራው ይተኩሳል፡፡ በዚህ ጊዜ ሁሉም ተደናግጠው ለመሸሽ ሲሞክሩ ከተማሪዎቹ ውስጥ ወንዶቹና ሴቶቹ ተለይተው እንዲቆሙ ትዕዛዝ ይሰጣል፡፡ ከ50 ተማሪዎች ውስጥ ሴቶች ባንድ ጥግ ቀሪዎቹ ወንዶች ደግሞ በሌላው ጥግ ይቆማሉ፡፡ ሊፓይን ወንዶቹ ከክፍሉ እንዲወጡ ካዘዘ በኋላ ‹‹እዚህ ክፍል ለምን ሽጉጥ ይዤ እንዳመጣሁ የሚነግረኝ አለ?›› በሚል ይጠይቃቸዋል፡፡ ከሴቶቹ ተማሪዎች አንዷ ‹‹አናውቅም›› ስትል መልስ ትሰጣለች፡፡ እሱም ‹‹I am fighting feminism›› ሴቶች የወንዶቹን ያህል መብት ይኑራቸው የሚለውን ሐሳብ ለመታገል ነው፤›› ሲል ያምባርቅባቸዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ከተማሪዎቹ አንዷ ‹‹ተመልከተን! እኛ የምሕንድስና ተማሪዎች ነን፡፡ መደበኛ ሕይወት ለመኖር የምናስብ እንጂ ሴቶች ከወንዶች የተለየ መብት ያግኙ ብለን ለመጮህ የተዘጋጀን ፌሚኒስት አይደለንም፤›› በማለት በማስተዛዘን ትመልስለታለች፡፡ ማርክ ሊፓይንም ‹‹እናንተ ሁላችሁም ሴቶች ናችሁ፡፡ ነገ መሐንዲስ ትሆናላችሁ፡፡ በወንዶችም ላይ ጣታችሁን ትቀስራላችሁ፡፡ እኔ ፌሚኒስትን እጠላለሁ፤›› በማለት ከግራ ወደ ቀኝ በመደዳው ተማሪዎች ላይ ይተኩሳል፡፡ ስድስቱን ይገድላል፤ ሦስቱን ያቆስላል፡፡ ከዚያም በኮሪደሩ ላይ፣ ወደ ሌላ ክፍል፣ አንደኛ ፎቅ ወደሚገኘው የኮሌጅ ካፍቴሪያ፣ ወደ ሦስተኛ ፎቅ እየተዘዋወረና እየተኮሰ ሰውን መጉዳት ተያያዘው፡፡ ከ20 ደቂቃ የተኩስ ቆይታ በኋላ ሊፓይን ጭንቅላቱ ላይ ተኩሶ ራሱን አጠፋ፡፡ በዚህች አጭር ደቂቃ 14 ሴቶችን (12 የምሕንድስና ተማሪዎችን፣ አንድ የነርሲንግ ተማሪና አንድ የዩኒቨርሲቲውን ሴት ሠራተኛ) ገደለ፡፡ አራት ወንዶችን ጨምሮ ሌሎች አሥራ አራት ሰዎችን አቆሰለ፡፡

ከአደጋው በኋላ ሊፓይን ራሱን ለማጥፋት ሲያስብ የጻፈው ደብዳቤና ለሌሎች ጓደኞቹ የጻፋቸው ሁለት ደብዳቤዎች በኪሱ ተገኝተዋል፡፡ ከደብዳቤዎቹ ይዘት ሊፓይን ፊሚኒስቶችን እንደሚጠላና ሊገደሉ ይገባል በሚል የአሥራ ዘጠኝ ታዋቂ ሴቶችን ስም ጽፏል፡፡ ሌፓይን ራሱ ምክንያታዊ እንደሆነ የሚገልጸው ይህ ደብዳቤ፣ ፌሚኒስቶች ሕይወቱን እንዳበላሹበት ይገልጻል፡፡ የሕይወት ታሪኩ እንደሚያሳየው ሊፓይን ከፈረንሳይ ተናጋሪ ካናዳዊ እናትና ከአልጀሪያዊ አባት የተወለደ ሲሆን፣ አባቱ ሴቶችን የሚንቅ፣ ሚስቱን የሚሳደብና የሚማታ፣ የእናትና የልጅን መልካም ግንኙነት የማይወድ ነበር፡፡ በሰባት ዓመቱ እናትና አባቱ የተለያዩ ሲሆን፣ ከእናቱ ጋር ሆኖ በቤተሰቦቿ አድጓል፡፡ ሊፓይን ጥሩ አዕምሮ የነበረው ግን ጭንቀት ያለበት ፌሚኒስቶትን የሚጠላ፣ ሙያ ያላቸውንና በተለይም ፖሊስነትን የመሰሉ ለወንድ መተው አለባቸው ብሎ የሚያስባቸውን ሥራዎች የሚሠሩ ሴቶችን የማይወድ እንደነበር ከሞቱ በኋላ የወጣ ሪፖርት ገልጿል፡፡
በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ማናቸውም ዓይነት መድሎን ለማስወገድ የተፈረመው ስምምነት (CEDAW) በአንቀጽ 1 በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት (Gender Based Violence) ሴቶች ሴት በመሆናቸው ብቻ የሚፈጸምባቸው ወይም በኅብረተሰቡ ሴቶችን በተለየ የሚመለከት ስለመሆኑ ይገልጻል፡፡ ጥቃቱ አካላዊ፣ አዕምሮአዊና ወሲባዊ ጥቃትን የሚያጠቃልል ሲሆን፣ ሴቶችን የማያስፈራራ፣ የሚያስገድድና ነፃነታቸውን የሚነፍግ ድርጊት ነው፡፡ በአገራችን ይህንን ትርጉም የሚያሟሉ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች መኖራቸው ለሁሉም ግልፅ ነው፡፡ በሀገራችን ሴቶችን የመጨፍጨፍ ድርጊቶች ባናስተውልም የሚደበደቡ፣ በስለት የሚወጉ፣ አሲድ የሚደፋባቸው፣ በብዙ ወንዶች የሚደፈሩ፣ በቤት ውስጥ ጥቃት የሚደርስባቸው፣ የሚሰደቡ፣ የሚለከፉ ብዙ ናቸው፡፡ እነዚህ የ16 ቀናት ንቅናቄ እነዚህ ድርጊቶች እንዲወገዱ ካልተቻለም እንዲቀንሱ ዓላማ ያደረገ ነው፡፡ ቀናቱም ካለፉ በኋላ በየዕለት ኑሮአችን ሴቶችን ከጥቃት የመንከባከብ ግዴታ በሁሉም ላይ ይጥላል፡፡












