፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ህዳር 17 2017| NBC ETHIOPIA -ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አሁን ያለው የኢትዮጵያ እውነት በአርአያነት የሚጠቀስ ፈጣን እድገት እንጂ ሚሊዮኖች የሚያልቁበት የረሀብ ታሪክ እንዳልሆነ ገለጹ።
በኢትዮጵያ በ1977ቱ ድርቅ ለተጎዱ ዜጎች ተቀንቅኖ ድጋፍ የተሰበሰበበት Do they know its Christmas? መዚቃ አሁን ላይ ዳግም መለቀቁ የኢትዮጵያን አሁናዊ የልማት ጉዞ ያላገናዘበ ገጽታን የሚያበላሽ ተረክ መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ በ1977 የተከሰተው ድርቅ ያስከተለውን ሰፊ ጉዳት ተከትሎ አይርላንዳዊው ሙዚቀኛ ቦብ ጊልዶፍና መሰል እውቅ ሙዚቀኞች ለኢትዮጵያ ድጋፍ ማድረግ የሚያስችል Do they know its Christmas? የሚል ሙዚቃ አቀንቅነው ከፍተኛ ድጋፍ አሰባስበዋል።
የዚህ የሙዚቃ 40ኛ ዓመት ዘንድሮ የተከበረ ሲሆን በወቅቱ የተሰራው ሙዚቃ ዳግም ተለቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የሙዚቃው 40ኛ ዓመት ሲዘከር ሙዚቃው ዳግም እንዲለቀቅ መደረጉ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እንደሚያመዝን ገልፀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን ላይ ኢትዮጵያ ሙዚቃው ላይ እንደተገለጸችው ሳይሆን በፈጣን እድገት ውስጥ የምትገኝ መሆኗን ገልጸዋል።
ሙዚቀኞቹ በወቅቱ የሰሩት ሥራ የሚያስመሰግናቸው ቢሆንም ሙዚቃው ዛሬ ላይ ከጊዜው ጋር አብሮ አለመሄዱ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ሊያመዝን እንደሚችል ጠቁመዋል።
ሙዚቃው የኢትዮጵያን አሁናዊ ሁኔታ ያቃለለና ሰዋዊነትን ዝቅ የሚያደርግ ተረክ የያዘ መሆኑንም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በፍጥነት እያደገ ያለ የኢኮኖሚ ባለቤት፣ ታሪካዊ የቱሪዝም መዳረሻ ሥፍራዎቿ ከሚጎበኙ ሥፍራዎች መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን እንዲሁም በአፍሪካ ትልቁን የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ እየገነባች ያለች ሀገር ሆና ብትታወቅ ይጠቅም ነበር ብለዋል።
ሙዚቃው አሁን እኛ ለምንፈልገው ኢንቨስትመንት የሚጠቅም አይደለም፤ ድርቅ አሁን ላይ እኛን አንደ አህጉርም እንደ ሀገርም አይገልጸንም ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ከዚህ በኋላ በረሃብ ልትታወቅ አትችልም ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጽንፆት ሰጥተዋል።
በኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ እና በሌሎች መስኮች እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች ዳግም ረሃብ እንዳይፈጠር የሚያደርጉ መሆናቸውንም ጠቅሰል።
ኢትዮጵያ በስንዴ ራሷን ችላለች፤ ሌሎች ምርቶችንም በሀገር ውስጥ ምርት የመተካት አቅም ፈጥራለች ብለዋል።
ኢትዮጵያ አሁን ላይ በአፍሪካ ሊጠቀስ የሚችል የግብርና ዘርፍ አብዮት እያካሄደች መሆኑንም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) መናገራቸውን ተናግረዋል ዘገባው የኢዜአ ነው፡፡












