፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨
የመስቀል በዓል ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ በኢትዮጵያውያን የሚከበር በዓል ነው። አከባበሩ ኅብራዊ ነው፤ የየአካባቢው ቀለም ይጨመርበታል፤የሚከበረው ግን በተመሳሳይ ወቅት ነው። ከግላዊ ይልቅ ቤተሰባዊና ማኅበራዊ በዓል ነው።
መስቀል ነባር ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን ያሳያል። በብዙ አካባቢዎች የዘመን መለወጫ በዓላት በመስከረም ወር፣ ከመስቀል በዓል ጋር ተያይዘው መከበራቸው ጥንታዊ ማኅበራዊ ትሥሥራችንን ሳያመለክት አይቀርም።
መስቀል በአስቸጋሪ፣ በፈታኝና በድንግዝግዝ ውስጥ ሆኖ ነገን የማየት ተምሳሌት ነው። ቅድስት ዕሌኒ በነበረችበት ዘመን መስቀሉ ተቀብሮ ነበር። እርሷም ከእምነት በቀር ዐቅም አልነበራትም።
አንድ ቀን መስቀሉን ከተቀበረበት ለማውጣትና ታሪኩን ለመቀየር ታስብ ነበር። ለዚህ ተምኔቷ ስትል ከማትፈልገው ሰው ጋር ኖረች። ደስ የማይላትን ሕይወት በትግልና በትጋት አለፈች።
በፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ተስፋዋን ቆስጠንጢኖስን ወልዳ አሳደገች። በታሪክ አልቆዘመችም። በነባራዊው ሁኔታ ተስፋ አልቆረጠችም። አይቻልምን ሳትቀበል፣ ከባድ ነውን ሳታምን ጉልበቷን በዓላማዋ ላይ አፈሰሰች። ትኩረቷን በሕልሟ ላይ አደረገች።
በመጨረሻም የማይቻለውን ቻለች፤ የማይሞከረውን አሳካች። የተቀበረውን የክርስቶስ መስቀል አወጣች። አንድ ብቻዋን የነበረች ሴት ዓለምን አስከተለች። የመስቀሉን ታሪክ ቀየረች።
የሚያዳክሙንን አንስማ፤ ተስፋ ለሚያስቆርጡን ልብ አንስጥ፤ በዙሪያችን ችግሮች አንወሰድ፤ በፈተናዎች ብዛት አንገረም። ትኩረታችንን በሕልማችን ላይ ብቻ እናድርግ። በመጨረሻ የድል ደመራውን መደመር የእኛ ይሆናል።
መልካም በዓል ይሁን።












