በአለማችን ለስደተኞች በጣም ውድ ከሆኑት ከተሞች አንዷ ናት፡፡አልፎ አልፎ "ሊዮንዳ" ወይም "ቅዱስ ፖል ዴ ሊዮንዳ" በመባል ትጠራለች የአንጎላዋ ዋና ከተማ ሉዋንዳ፡፡ ከአፍሪካ ጥንታዊ የቅኝ ግዛት ከተሞች መካከል እና ከአንጎላ አምስት ሜትሮፖሊታን ከተሞች አንዷም ናት ሉዋንዳ፡፡ በሰሜናዊ አንጎላ በአትላንቲክ የባሕር ዳርቻ ላይ የምትገኘው ይህች ከተማ የአገሪቷ ትልቋ ከተማና ከተጨናነቁ የባህር ወደቦች መካከል አንዷም ጭምር ናት፡፡እንዲሁም የኢንዱስትሪ፣ የባህል እና የፖለቲካ ብሎም የቱሪስት ማዕከልም ናት፡፡ ከተማዋ በአውሮፓያውያኑ አቆጣጠር 1576 በፖርቹጋላዊው አሳሽ ፓኦሎ ዲያስ ዲ ኖቫስ እንደተቆረቆረችና እና በ1627 ፓርፖርቹጋላውያን ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሰፈሩባት ታሪኳ ያስረዳል፡፡ በዚህም የፖርቹጋል ቅኝ ግዛት አስተዳደር ማዕከል ብሎም የባሪያ ንግድ ወደብ በመሆን እስከ 1836 አገልግላለች፡፡ በ1975 ከፖርቹጋል ቅኝ ግዛት ነፃ ስትወጣ የነፃዋ አንጎላ ዋና ከተማ ሆነች። በ21 ኛው ክፍለ ዘመን ከተማዋ ትልቅ የመልሶ ግንባታ ስራ ላይ ስትሆን የከተማዋን ገጽታ በእጅጉ የሚቀይሩ ብዙ አዳዲስ ትላልቅ እድገቶች እየተከሰቱባት ነው፡፡

ሉዋንዳ ሞቃታማ የአየር ንብረት ያላት ሲሆን በሀገሪቱ በጣም ተወዳጅ የቱሪስት መዳረሻ ናት፡፡
ታሪካዊ እና ሰማይ ጠቀስ ፎቆቿ እንዲሁም ሰፋፊ መንገዶቿ ሉዋንዳን ዘመናዊ መልክን ሰጥቷታል፡፡ የሀገሪቱ ትልቅና ዋና የኢኮኖሚ ማዕከል የሆነችው ሉዋንዳ ታሪካዊ ሙዚየሞች ፤ብሄራዊ ፓርኮች ፤ሲኒማ ቤቶች ፤ባህር ዳርቻችን ጨምሮ በርካታ የጎብኚዎች መዳረሻዎችንበውስጧ ይዛለች፡፡በዛሬው የመዳረሻ ሰአታችን ጥቂቶቹን ልንንግራችሁ ወደናል፡፡
ከአንጎላ ዋና ከተማ ሉዋንዳ 40 ኪሜ ወይም 25 ማይል ርቀው ቢጓዙ ቀልብን የሚስብ አስደናቂ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ያለው ውብ ስፍራ ያገኛሉ….ሚራዶሮዳ ሉዋ፡፡ ይህ ስፍራ የተለያየ ቀለም ያላቸው የድንጋይ ክምችቶች ገደል ነው። ሚራዶሮ ዳ ሉዋ ከፖርቱጋልኛ ቃል የተተረጎመ ሲሆን “የጨረቃ እይታ” የሚል ትርጓሜም አለው፡፡
ስፍራው ከጊዜ በኋላ በንፋስ እና በዝናብ ምክንያት በተከሰተው የአፈር መሸርሸር ሳቢያ ዛሬ የምናየው አስገራሚና ልዩ ገጽታን ፈጥሯል፡፡
ስፍራው በርካታ የሀገር ውስጥ ብሎም የውጭ ጎብኚዎች አብዝተው ለማየት የሚመርጡት ማራኪ እይታ ያለው ገደላማ መስህብ ነው፡፡
እንደ ሰይፍ የተሳሉ የሚመስሉት ሸለቆዎቹ እና አስደናቂ መልክዓ ምድሩ ይበልጥ ውበቱ የሚገለጠው ጀንበር ስትጠልቅ ነው ፡፡ ጎብኚዎችም ከጨረቃ በቅርብ ርቀት እንዳሉ እንዲሰማቸው ያደርጋል።

ከሉዋንዳ በቅርብ ርቀት የሚገኘው የሙሱሉ ደሴት ጎብኚዎች ቅዳሜና እሁድን ጨምሮ የእረፍት ቀናትን ለማሳለፍ የሚመርጡት ሌላኛው ተወዳጅ ውብ ስፍራ ነው ፡፡ ከሉዋንዳ በስተደቡብ የሚገኘው የሙሱሉ ደሴት በአንጎላ ታዋቂ የቱሪስት መስህብ ስፍራዎች መካከል ተጠቃሽ ነው፡፡ ይህ ባህር ዳርቻ በአትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ የተዘረጋ ሲሆን በግምት 30 ኪ.ሜ ርዝመት እንዳለው ይነገራል፡፡ በነጭ አሸዋማ የባህር ዳርቻዎች እና ንጹህ ውሃ የሚታወቀው የሙሱሎ ደሴት ለተፈጥሮ አፍቃሪዎች እና የውሃ ስፖርት ወዳዶች መዳረሻ ነው፡፡ በጀልባ ሽርሽር ለመዝናናት ፤ የባህር ዳርቻ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ እንዲሁም የውሃው ጥልቀት አነስተኛ በመሆኑ እንደልብ ለመዋኘት አመቺ ነው፡፡ ማረፍ ከፈለጉም ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች እና ምግብ ቤቶች በብዙ አማራጭ ያገኛሉ፡፡ በዚህም የቱሪስቶች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱን ነው መረጃዎች የሚያመላክቱት፡፡
በሉዋንዳ ከተማ በሞሮ ዳ ክሩዝ ውስጥ የሚገኘው ብሔራዊ የባርነት ሙዚየም አንጎላውያን ለ500 ዓመታት በባርነት የቆዩበትን ፤ ተጎጂዎችን ለማሰብ እና ለዘመናት የተፈጸሙትን አስከፊ ድርጊቶች በጋራ ለማስታወስ የተዘጋጀ ነው፡፡
እ.ኤ.አ በ1997 የተመረቀው ይህ መታሰቢያ ሙዚየም በባሪያ ንግድ ወቅት ጥቅም ላይ የዋሉ ውድ ዕቃዎችን ፤ ፎቶግራፎችን ይዟል። በተጨማሪ ብሔራዊ የባርነት ሙዚየም ብዙ መስህቦች አሉት፡፡ በሀገሪቱ የነበረውን የባሪያ ንግድ ታሪክ በመግለጽ የሚያሳዩበትን የቲያትር ተውኔቶች፤ የግጥም ፣ የሙዚቃ ፤ የአውደ ጥናቶች የሚቀርቡበትና የሚታዩበትም ስፍራ አለው ፡፡
በአንጎላ የባሪያ ንግድን እና የግዳጅ ሥራን ለማስታወስ የተመሰረተው ይህ ሙዚየም በአሁኑ ጊዜ በአንጎላ በብዛት ከሚጎበኙ ሙዚየሞች አንዱ ሲሆን በወር እስከ ሁለት ሺህ ሦስት መቶ ጎብኚዎች ወደ ሥፍራው ያቀናሉ፡፡












